የሀገር ውስጥ ዜና

በከተማዋ አውቶቡሶች እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት እየተሰጠ ነው

By sosina alemayehu

April 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በቀን እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት እየሰጠሁ ነው አለ።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አካሉ አሰፋ ከነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ አላስፈላጊ መጉላላቶች እና ችግሮች እንዳይኖሩ እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህም የተማሪዎችን ጨምሮ በ212 መስመሮች 1 ሺህ 200 አውቶቡሶች እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በየቀኑ ከ1 ነጥብ 4 እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን እያመላለስን ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው÷ ይህም ከባለፉት ጊዜያት አንጻር እስከ 300 ሺህ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

የአውቶቡስ የምልልስ፣ የመጫን አቅም እና የኪሎ ሜትር ሽፋን ማደጉን ጠቅሰው÷ አንድ አውቶቡስ በቀን በትንሹ 13 ምልልሶች እንዳሉትና አማካይ የኪሎ ሜትር ሽፋኑም 160 መድረሱን አስረድተዋል።

በአውቶቡሶቹ ላይ ጂፒኤስ በመግጠም የት እንዳሉ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንና ከተፈቀደላቸው ሰዓት በላይ እንዳይቆሙ ክትትል እንደሚደረግባቸው ጠቁመዋል።

በመሳፍንት እያዩ