ዓለምአቀፋዊ ዜና

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ሊወያዩ ነው

By Melaku Gedif

April 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመነጋገር ሩሲያ ገብተዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለሁለት ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማቆም መደራደር ከፈለገች ስልክ መደወል እና ወደ እኛ መምጣት ይጠበቅባታል ብለዋል።

ከሰሞኑ ፓኪስታን የነበሩት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ሳይነጋገሩ ከፓኪስታን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተው ሀገሪቱን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩ ሀገራቸው ለድርድር ያሏትን አቋሞች ለፓኪስታን ባለሥልጣናት አሳውቀው ወደ ኦማን አቅንተው የነበረ ሲሆን÷ ዛሬ ደግሞ ሩሲያ ገብተዋል።

በሞስኮ በሚኖራቸው ቆይታም ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህንን ተከትሎም ዶናልድ ትራምፕ ኢራን መደራደር ከፈለገች ወደ እኛ መምጣት አለባት ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሩሲያ ጉዞ ቴህራን የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ፍለጋ አካል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በብርሃኑ አበራ