የሀገር ውስጥ ዜና

በሀገር ውስጥ መድኃኒት የማምረት አቅምን ለማሳደግ…

By Adimasu Aragawu

April 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓቶች እና መድኃኒቶችን ለማምረት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከማድረግ ጀምሮ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም የተለያዩ መድኃኒቶች እና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ እየተመረተ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እየዋለ ነው።

መድኃኒትን በራስ አቅም ለማምረት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ሀገሪቱ የምትጠቀመውን የመድኃኒት ፍጆታ እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ በአፍሪካ ደረጃ የማይመረቱ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እና ለአፍሪካ የመድኃኒት ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ መድኃኒቶች የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከል በቅርቡ በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መድኃኒት፣ ልብስ እንዲሁም ምግብ በበቂ አምርቶ የራሱን ፍጆታ የማይሸፍን ሀገር እንደሀገር ሉዓላዊ ሀገር ነኝ ብሎ መቀጠል እንደማይችል በዚህ ወቅት መግለፃቸውም የሚታወስ ነው።

በዚህም ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት መሰረታዊ ጉዳዮች በመሆናቸው በእነዚህ ሦስቱ ላይ ዕቅድ በመያዝ በመንግስት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በመድኃኒት ኢትዮጵያ ለራሷ የሚያስፈልጋትን ማምረት አለባት የሚል እምነት በመያዝ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

መድኃኒቶችን በራስ አቅም ማምረት ለነገ የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሰሩ ስራዎች መድኃኒት እና የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ተችሏል፡፡

በዚህም በሀገር ውስጥ የሚመረተውን የህክምና ግብዓት አሁን ላይ 44 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ከ25 በላይ ኩባንያዎች በመድኃኒትና በሕክምና ግብዓት ምርት በንቃት እየተሳተፉ ሲሆን÷ ይህም በሀገር ውስጥ የሚመረተውን የህክምና ግብዓት በመሸፈን በየዓመቱ ከ53 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ጫናን መቀነሱ ተመላክቷል።

በወንድማገኝ ጸጋዬ