አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር በሴንት ፒተርስበርግ ተወያይተዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመነጋገር ዛሬ ጠዋት ሩሲያ መግባታቸው ይታወቃል።
የኢራን ከፍተኛ ዲፕሎማት አባስ አራግቺ በሩሲያ ቆይታቸውም ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
በኢራን በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን እና በሞስኮ የኢራን አምባሳደርን ያካተተ ነው።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ቀደም ሲል እንዳሉት÷ ውይይቱ በኢራን እና በመካከለኛው ምስራቅ ካሉት ወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር በጣም አስፈላጊ ነው።
የኢራን ልዑክ ወደ ሩሲያ ማቅናቱን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን መደራደር ከፈለገች ወደ እኛ መምጣት አለባት ማለታቸው ይታወሳል።
በብርሃኑ አበራ