የሀገር ውስጥ ዜና

ቢሊየን ዶላሮችን ያዳነው ንቅናቄ…

By Hailemaryam Tegegn

April 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከተል የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ከግብ ለማድረስ በአስደናቂ ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ የበጋ ስንዴ ልማትን በማስተዋወቅ በስንዴ ራስን ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የቻለችበት ጅምር አይነተኛ ምሳሌ ተደርጎ የሚቀርብ ነው፡፡

በተጨማሪም ከውጭ ከሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ጥገኝነት ተላቅቃ ራስን በመቻል ብቻ ሳትገደብ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በአስደናቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር ሂደት ላይ ትገኛለች፡፡

ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት ረገድ ገና ከጅምሩ ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡበት ሆኗል፡፡

በንቅናቄው አማካኝነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተዘጉ ፋብሪካዎችን ዳግም ሥራ በማስጀመር፣ ምርታማነትን በማሳደግና በስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ገቢ ምርቶችን በመተካት በቢሊየን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በተለይም በተኪ ምርቶች ረገድ ባለፉት 9 ወራት ብቻ 4 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ምርት በሀገር ውስጥ ተመርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ብቻ ሳይሆን ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ርዕይን ያነገበ ነው፡፡

ባለፉት 9 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች 433 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በፈጣን የሽግግር ሂደት ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ 830 ፋብሪካዎችን ዳግም ስራ ለማስጀመርና የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የማምረት አቅም እንዲያድግ ንቅናቄው ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶችን በማላቅ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ በተለይም የፋይናንስ እና የኃይል አቅርቦት ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ