የሀገር ውስጥ ዜና

ነዋሪዎችን ከጤና መጓደልና ከአደጋ ስጋት የታደገው የወንዝ ዳርቻ ልማት…

By Hailemaryam Tegegn

April 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነው የወንዝ ዳርቻ ልማት ለጤና ስጋት የነበሩ አከባቢዎችን ወደ ምቹ የመዝናኛ ቦታነት ተቀይረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለበርካታ ነዋሪዎች ንብረት እና ሕይወት መጥፋት ምክንያት የነበሩ ስፍራዎች አሁን ላይ በአረንጓዴ ልማት አጊጠዋል።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ሳቢ፣ ማራኪ፣ ለከተማ ነዋሪ ምቹ በማድረግ እና በማስተዳደር በኩል ብዙ ሀገራት የተሻለ ልምድ እና ተሞክሮ እንዳላቸው ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያ በለውጡ አመታት በትኩረት ከተሰራባቸውና ውጤት ከተገኘባቸው ስራዎች መካከል የወንዝ ዳርቻ ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡

በዚህም በአዲስ አበባ ከቀበና ድልድይ እስከ እንጦጦ ተራራ ያለው የወንዞች ዳርቻ ልማት ለዚህ በጎ ተግባር በአብነት ተጠቃሽ ከሆኑት ፕሮጀክቶች መካከል ዋነኛው ነው፡፡

በከተማዋ የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻ መጣያ የነበሩት እነዚህ ወንዞች በዙሪያቸው ለሚኖሩ ዜጎች የአደጋ ስጋትና የጤና ጠንቅ ሆነው ቆይተዋል፡፡

ከተማዋ አስደናቂ ገጽታን እንድትላበስ ያስቻለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ከከተማ ውበት ባሻገር የዜጎችን አኗኗር የማሻሻል ላቅ ያለ ዓላማን ያነገበ ነው፡፡

በዚሁ የልማት ተነሳሽነት አማካኝነት ወንዞችን ንጹህ በማድረግ ውብ መናፈሻዎች የተገነቡ ሲሆን፥ ለወጣቱ የሥራ ዕድል የፈጠረና የይቻላል ሀሳብን የገነባ ልማት መሆኑ ይወሳል፡፡

እነዚህን የልማት ስራዎች ተከትሎ የንግድ ቦታዎች የተስፋፉ ሲሆን፥ ወንዞችን የሚያገናኙ በርካታ ድልድዮች በዚህ የወንዝ ዳርቻ ልማት መገንባታቸው የሚጠቀስ ጉዳይ ነው፡፡

ልማቱ ያመጣውን ትሩፋት በአግባቡ መጠቀም፣ በባለቤትነት ስሜት መጠበቅና ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲስፋፋ ማድረግ ከኅብረተሰቡ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማቱን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

በጠቃላይ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ብክለትን በመከላከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለነዋሪዎች እያስገኙ ሲሆን፥ ማህበረሰቡም ልማቱን በመጠበቅና በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

በአቤል ነዋይ