የሀገር ውስጥ ዜና

ሚኒስቴሩ ለቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የሚውሉ 92 የኤሌክትሪክ ገልባጭ መኪኖችን ስራ አስጀመረ

By Adimasu Aragawu

April 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ 92 የኤሌክትሪክ ገልባጭ መኪኖችን ስራ አስጀምሯል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ መኪኖች የመተካት ስራ በከፍተኛ ፍጥነት እያከናወነች ነው፡፡

ይህም ሀገሪቱ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ለዘላቂ ልማትና ለታዳሽ ኃይል የሰጠችውን የላቀ ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና የዜጎችን የትራንስፖርት ወጪ ለመቆጠብ ጭምር እየሰራች እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

አዲስ የገቡት የኤሌክትሪክ ገልባጭ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እንደሚውሉ ገልጸዋል፡፡

መኪኖቹ ከቀረጥ ነጻ የገቡ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው÷ ሲሲሲሲ የተሰኘ የቻይና ካምፓኒ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን አስረድተዋል፡፡

በመቅደስ ከበደ