የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ወታደራዊ ትብብር ለማሸጋገር ፍላጎት አላቸው 

By Mikias Ayele

April 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መከላከያ ሚኒስቴር ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ ያላቸውን ታሪካዊ ትስስር ወደ ላቀ ስልታዊ ወታደራዊ ትብብር ለማሸጋገር ግልፅ ፍላጎትና ዕቅድ አላቸው አለ።

በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ እና ከፍተኛ ልዑካቸው በመከላከያ ሚኒስቴር ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።

በዚህም ከመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) እና ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያይተዋል።

አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና የሞዛምቢክ ግንኙነት በነፃነት ትግል ወቅት በደም የተፈተነ ታሪካዊ ወንድማማችነት ነው።

ኢትዮጵያ ለሞዛምቢክ ነፃነት ያበረከተችው አስተዋጽኦ የፓን አፍሪካኒዝም መርህ ቀዳሚ መገለጫ መሆኑን አስታውሰዋል።

አሁን ያለውን ታሪካዊ ትስስር ወደ ላቀ ስልታዊ ወታደራዊ ትብብር ለማሸጋገር ግልፅ ፍላጎትና ዕቅድ መኖሩን አመልክተዋል።

ፕሬዚዳንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሞዛምቢክ ሉዓላዊነትና ነፃነት ያበረከተችውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያለውን የላቀ የውጊያ ብቃትና የዝግጁነት ደረጃ አድንቀዋል።

ጉብኝቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸውም ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር በወቅታዊ ቀጣናዊ የፀጥታ ጉዳዮችና በሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ስትራቴጂዎች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሀገራቱ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከማጠናከር ባለፈ ለአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተመልክቷል።