የሀገር ውስጥ ዜና

በለውጡ ዓመታት ከ19 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል – ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

By Adimasu Aragawu

April 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ዓመታት ለ19 ሚሊየን 872 ሺህ 846 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል አሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል።

ሚኒስትሯ “የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀውና በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች በሚቀርቡበት የምክክር መድረክ ላይ በስራና ክህሎት ዘርፍ በለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ስኬቶች አብራርተዋል።

በማብራሪያቸውም÷ ዘርፉ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት በማድረግና ብቁ የሰው ሀብት እንዲሁም ምቹ እና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የተፈጠረባት ኢትዮጵያን ለማየት መታለሙን አስረድተዋል።

በዚህም ከለውጡ በኋላ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የስራ ስመሪት እንዲሁም ዜጎች በቤት ውስጥ እና ባሉበት ሆነው በሚሰሯቸው ስራዎች አማካኝነት ለ19 ሚሊየን 872 ሺህ 846 ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል ማለታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

ይህን ታላቅ ስኬት ለማስመዝገብ ያስቻለው ኢንተርፕርነር ተቋማትን በመፍጠር፣ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር፣ የቢዝነስ መስፋፋት እና የልህቀት ማዕከላት በማሳደግ፣ ቲቬት ዲጂታላይዜሽን በማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች በመተግበራቸው የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።