የሀገር ውስጥ ዜና

ኅብረተሰቡ ነዳጅን ከመቆጠብ ባለፈ ኮንትሮባንድን በመታገል የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Adimasu Aragawu

April 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኃይል ሉዓላዊነት ጉዞ ከአስከፊ አደጋ የታደገን በመሆኑ ኅብረተሰቡ ነዳጅን ከመቆጠብ ባለፈ ኮንትሮባንድን በመታገል የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

አገልግሎቱ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ከቀውስ ባሻገር መሻገር

በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትና በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት ዓለም አቀፉ የነዳጅ አቅርቦት ተቋርጦ፣ የበርካታ ሀገራት ማደያዎች እየተዘጉና ማኅበራዊ ቀውሶች እየተባባሱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ይህንን ከባድ ፈተና መቋቋም የቻለችው መንግሥት ላለፉት ስምንት ዓመታት በታዳሽ ኃይል (ውኃ፣ ነፋስ፣ ፀሐይና ጂኦተርማል) ላይ ባከናወናቸው ግዙፍ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች ነው።

የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል አማራጮችና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) ንቅናቄ ዛሬ የሕልውናችን ዋስትና ሆነዋል። እነዚህ መሠረተ-ልማቶችን መንግሥት አስቀድሞ ዝግጅት ባያደርግባቸው ኖሮ ሀገሪቱ በከፋ የኢኮኖሚ መሽመድመድና የዋጋ ንረት ውስጥ ትወድቅ ነበር። የጎዴ የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያም የኢነርጂ ሉዓላዊነታችንን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊውል የነበረን በጀት የዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት ጫና በዜጎች ላይ እንዳይበረታ በሚል በቢሊዮን የሚቆጠር የነዳጅ ድጎማ እያደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ ይህ ድጎማ ለኮንትሮባንድና ለጥቁር ገበያ ዓላማ እንዲውል አይፈቀድም። የነዳጅ ኮንትሮባንድን መከላከል የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት ከጸጥታ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል።

በአጠቃላይ የጀመርነው የኃይል ሉዓላዊነት ጉዞ ከአስከፊ አደጋ የታደገን በመሆኑ ኅብረተሰቡ ነዳጅን ከመቆጠብ ባለፈ ኮንትሮባንድን በመታገል የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል። የዛሬው መዋቅራዊ ሽግግራችን ለነገው ዘላቂ ብልጽግና መሠረት ነው።