አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመኸር እርሻ የሚውል የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ በተለያዩ የግብርና ሰብሎች ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም የግብርና ሜካናይዜሽንን ከማስፋፋት ጀምሮ አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶችን ማሰራጨት ላይ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በዘንድሮው መኸር እርሻ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት እንደሚለማ ጠቁመው÷ ለዚህም ከ14 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የሚሆነው ወደ ክልሉ ገብቶ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
በአሁኑ ወቅት 2 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች መሰራጨቱን አስረድተዋል፡፡
ቀሪውን የአፈር ማዳበሪያ በተገቢው ሰዓት ለማዳረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል አስፈላጊ የቁጥጥር ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስገንዝበዋል፡፡
ለመኸር እርሻ የሚውለው የአፈር ማዳበሪያ በተገቢው ሰዓትና ሁኔታ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ሕብረተሰቡ በአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ላይ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥም አቶ በሪሶ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ