አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስምንት ዓመታት ከፍተኛ ስኬት ከተመዘገበባቸው እና ዐበይት ውጤቶች ከተገኘባቸው ማህበራዊ ዘርፎች መካከል ትምህርት ይጠቀሳል።
በትምህርቱ መስክ ከተገኙ ትውልድ ተኮር እመርታዎች አንዱ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው እና የማህበራዊ ዘርፍ ውጤቶች በቀረቡበት የምክክር መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ በእጅጉ የተጎዳ እንደነበር አንስተዋል።
በዚህም በጥናት በተደገፈ መልኩ የትምህርት ዘርፉን ፍላጎቶች እና ተግዳሮቶች በመለየት ከተመዘገቡ ዋና ዋና ለውጦች መካከል የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ማሳደግ አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት በዘርፉ የተወሰደ ቁልፍ የማስተካከያ ርምጃ ሲሆን፤ ዘመናዊና ትውልድ ገንቢ ለማድረግ በትኩረት ተሰርቷል የሚሉት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ከነበረበት 4 ሺህ 840 ከ34 ሺህ በላይ ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት የህፃናትን የአካል፣ የአዕምሮ፣ የስሜትና የማህበራዊ ግንኙነትን የሚያሳድግ እንደመሆኑ ልዩ ትኩረትን ይሻል።
ህፃናት በትምህርታቸውና በህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያስፈልጋቸውን ክህሎትና እውቀት በማስጨበጥ ለዘላቂ ትምህርትና ለግል ስኬታማነት መሰረት ይጥላል።
በዚህም በኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ጥራት ያለው የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ መምህራንን ለማሰልጠን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ የመማሪያ አካባቢን ለመፍጠር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ተቋቁመዋል፤ እየተቋቋሙ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በእነዚህ የመጀመሪያዎቹ የህፃናት እድገት ዓመታት ላይ ሀብት በማፍሰስ፣ በራሱ የሚተማመን፣ የበቃ፣ ንቁ እና ተራማጅ የሆነ ትውልድ በመፍጠር የረጅም ጊዜ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን እያሳለጠች ትገኛለች።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ህጻናት ችሎታቸውን የሚለዩባቸው፣ የሚያዳብሩባቸው እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት እንደፍላጎታቸው ትምህርት የሚያገኙባቸው የማህበራዊ ልማት እመርታ እንደመሆናቸው መጠን ለሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
በብርሃኑ አበራ