የሀገር ውስጥ ዜና

በፓርቲዎች መካከል የውይይት ባህልን ለማዳበር…

By Adimasu Aragawu

April 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓርቲዎች መካከል የውይይት እና ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር እየሰራን እንገኛለን አለ የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዘሪሁን ኮርሜ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ÷ ምክር ቤቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የውይይት እና ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር እየሰራ ነው።

ዜጎች በመራጮች ምዝገበ ወቅት ያሳዩትን ተነሳሽነት በማስቀጠል በምርጫው ዕለት ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መኖር ለጠንካራ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው÷ ምርጫው ነጻ፣ ተዓማኒና ሰላማዊ እንዲሆን ምክር ቤቱ የጋራ አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

ምርጫ ቦርድ እስካሁን የመጣበትን መንገድ በማስቀጠል ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰበሳቢ ማሩ ጃኔ በበኩላቸው÷ ምርጫ ለሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት መሆኑን በጽኑ እናምናለን ብለዋል።

ፓርቲዎች ከምርጫ በፊትና በኋላ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየሰራን እንገኛለን ያሉት ሰብሳቢው÷ ምክር ቤቱ ከምርጫ ቦርድ እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምክር ቤቱ መኖር የፈጠራቸው እድሎች እና የፈታቸው ተግዳራቶች የሚያበረታቱ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

በመራዖል ከድር