ቴክ

ከ50 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፍ ተቻለ

By Adimasu Aragawu

April 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በ9 ወራት የተሰነዘሩ ከ50 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፍ ተችሏል አሉ።

ዋና ዳይሬክተሯ በተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ወቅት እንዳሉት÷ አስተዳደሩ የጥቃት ሙከራዎችን በማክሸፍ የዲጂታል ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ስራውን በብቃት እየተወጣ ነው።

አፈጻጸሙ ሀገሪቱ የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ስትራቴጂያዊ ራዕይ ከማሳካት፣ ብሔራዊ ደህንነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ያላትን ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ ከማሳደግ አኳያ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑ ተገልጿል።

ባለፉት 9 ወራት በሀገሪቱ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችና ተቋማት ላይ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በተደረገው የነቃ የ24 ሰዓት ክትትልና በተዘረጋው የላቀ የመከላከል አቅም 99 በመቶ የሚሆኑ ጥቃቶችን ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ መቻሉ ተመላክቷል።

የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ የመለየት፣ የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት አቅምን በማዘመን ፈጣንና ቀልጣፋ የኦፕሬሽን ስራዎች መከናወናቸውም በመድረኩ ተነስቷል።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር በራስ አቅም ለመምራትና የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርቶችን እና መፍትሄዎችን የማልማትና ለተለያዩ ተቋማት የማስታጠቅ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢመደአ መረጃ አመላክቷል።