አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራ አጥነትን ችግር በዘላቂነት መፍታት ካልተቻለ እንደ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ይታወቃል።
ስለሆነም የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በማተኮር ምቹ እና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የተፈጠረባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “የማህበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው የምክክር መድረክ በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች ቀርበዋል።
በመድረኩ በሥራ እድል ፈጠራ የተገኙ ስኬቶች ተብራርተዋል።
በዚህ ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፤ በለውጡ ዓመታት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዲሁም በርቀት ሥራዎች አማካኝነት ለ19 ሚሊየን 872 ሺህ 846 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል።
ይህ ታላቅ ስኬት የተመዘገበው ኢንተርፕርነር ተቋማትን በመፍጠር፣ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር፣ የቢዝነስ መስፋፋት እና የልህቀት ማዕከላት በማሳደግ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን ዲጂታላይዜሽን በማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች በመተግበራቸው እንደሆነም አንስተዋል።
ይህ ዘርፍ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት በማድረግና ብቁ የሰው ሀብት እንዲሁም ምቹ እና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የተፈጠረባት ኢትዮጵያን ለማየት ያለመ በመሆኑ የለውጡ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከሰሞኑ የ2018 በጀት ዓመት የ100 ቀናት ግምገማ እና የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ የሥራ እድል ፈጠራ ባለፉት ዓመታት በአማካኝ 22 በመቶ እድገት አሳይቷል።
ባለፉት 9 ወራት ብቻ 4 ሚሊየን 320 ሺህ የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 3 ሚሊየን 250 ሺህ የሥራ እድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።
አፈጻጸሙ በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ መሆኑን በመግለጽ፤ የግብርና፣ የአገልግሎት እና የኢንዱስትሩው ዘርፍ የሥራ እድል በመፍጠር ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
በውጭ ሀገራት ሕጋዊ የሥራ እድሎችን መፍጠር፣ ክህሎት መር አሰራር፣ የኢንተርፕራይዝ አዋጅ በአዲስ መልክ መውጣቱ፣ ሥራ ፈላጊዎችን በዲጂታል ስርዓት መመዝገብ መቻሉ እና ሌሎችም ለውጤቱ መምጣት የጎላ ሚና ተጫውተዋል።
በብርሃኑ አበራ