ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና ከ53 የአፍሪካ ሀገራት ጋር የምታደርገውን ግብይት ከታሪፍ ነፃ ልታደርግ ነው

By Mikias Ayele

April 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና የዲፕሎማሲ አጋሮቼ ካለቻቸው 53 የአፍሪካ ሀገራት ጋር የምታደርገውን የንግድ ግብይት ከነገ ጀምሮ ከታሪፍ ነፃ ታደርጋለች፡፡

ቻይና ቀደም ሲል በማደግ ላይ ላሉ 33 ሀገራት ከታሪፍ ነፃ የሆነ የንግድ ፖሊሲን ተግባራዊ አድርጋ የነበረ ሲሆን፤ 20 ተጨማሪ ሀገራት በማከል ከነገ ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ከታሪፍ ነጻ  ግብይት በ53 የአፍሪካ ሀገራት ለመተግበር ውሳኔ አሳልፋለች፡፡

ውሳኔው ቻይና ከአፍሪካ አኅጉር ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ እና የአፍሪካን ኢኮኖሚ ተገማች እና የተረጋጋ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ፤ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት ቻይና ከአፍሪካ ጋር የገነባችው የንግድ እና ሌሎች ትብብሮች በአፍሪካ ኢኮኖሚ እና በቻይና እድገት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል፡፡

የቻይና ኢኒሼቲቮች እየተፈተነ ባለው የዓለም ንግድ ስርዓት ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት የሚያጋጥማቸውን ኢ-ፍትሐዊነት በመከላከል የልማት ችግሮቻቸውን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም አንዳንድ ሀገራት በታዳጊ የአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ላይ በተናጠል የሚጥሉት ከፍተኛ ታሪፍ ኢኮኖሚያቸው እንዳይረጋጋ የሚያደርግ ሲሆን፤ ቻይና በተቃራኒው ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ከታሪፍ ነፃ አድርጋለች፡፡

በፈረንጆቹ 2025 የቻይና እና አፍሪካ የንግድ ግንኙነት 348 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን፤ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የ17 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

በዚህም ቻይና በአሁኑ ወቅት ከሌሎች የዓለም ሀገራት በበለጠ የአፍሪካ ቀዳሚ የንግድ አጋር በመሆን፣ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ግንባታና የኢኮኖሚ ትብብር እያደረገች ትገኛለች።

ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በደቡብ ለደቡብ ትብብር እንዲሁም የትብብር ፎረም በሆነው የቻይና አፍሪካ ትብብር (ፎካክ) አማካኝነት በጋራ እየሰራች መሆኗ ይታወቃል።

በሚኪያስ አየለ