የሀገር ውስጥ ዜና

የትምህርት ዘርፍ ስብራቶችን ለመጠገን ትውልድን የታደጉ ርምጃዎች ተወስደዋል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Melaku Gedif

April 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት በትምህርት ዘርፍ የታዩ ስብራቶችን ለመጠገን ትውልድን የታደጉ ስትራቴጂካዊ ርምጃዎችን ወስዷል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

መንግሥት በትምህርት ዘርፍ የታዩ ስብራቶችን ለመጠገን ትውልድን የታደጉ ስትራቴጂካዊ ርምጃዎችን ወስዷል።

የለውጡ መንግሥት ሀገራዊ ኃላፊነትን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ በትምህርት ዘርፉ ላይ ሲንከባለል የመጣው ትልቁ ስብራት “የመሠረት መናጋት” መሆኑን በጥልቀት በመለየት፣ ይህንን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ትውልድ ተኮር የሆኑ ሪፎርሞችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

በተለይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ያለምንም የቅድመ-መደበኛ ዝግጅት በቀጥታ ወደ አንደኛ ክፍል በመግባታቸው ምክንያት፣ በትምህርት ገበታ የመቆየትና እውቀት የመቅሰም አቅማቸው ተዳክሞ ቆይቷል።

ይህንን የጠና ህመም ለመፈወስ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ34 ሺህ በላይ የቅድመ-መደበኛ (O-Class) ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ታሪካዊ የሆነ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አከናውኗል። ይህ እርምጃ የሕፃናትን አእምሯዊና ስነ-ልቦናዊ ዝግጁነት ከማረጋገጡም ባለፈ፣ በተለይም በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ዜጎች ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነትን የፈጠረ እና ለሀገሪቱ የሰው ኃይል ግንባታ ወሳኝ የሆነ የለውጥ ምሰሶ ነው።

የትምህርት ጥራትን ከምንጩ ለማስተካከል መንግሥት የነደፈው አዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት ተማሪዎች ከንድፈ-ሐሳብ ባለፈ በተግባርና በምርምር እንዲታነጹ የሚያስችል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በትምህርት ጥራት ላይ ተደቅኖ የነበረውን የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት እጥረትና የተዛባ ስርጭት ለመቅረፍ መንግሥት በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ፣ እስካሁን 279 ሚሊዮን የሚጠጉ መጽሐፍትን ለየደረጃው በማዳረስ የዘመናት የመጽሐፍ ችግርን መቅረፍ ችሏል።

በቀጣይ ዓመትም “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” የሚለውን አገራዊ ግብ ለማሳካት የተያዘው ጽኑ አቋም፣ ተማሪዎች በራሳቸው የማንበብና የመመራመር አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ይህም በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ላይ የታየውን ዝቅተኛ ውጤት በዘላቂነት ለመቀየርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ዜጋን ለማፍራት የተያዘ ስትራቴጂክ የመፍትሔ እርምጃ ነው።

ትምህርት ጥራት የሚኖረውና ፍሬ የሚያፈራው ተማሪው አካላዊና አእምሯዊ ሰላም ሲኖረው ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፣ መንግሥት “የትምህርት ቤት ምገባ” ፕሮግራምን እንደ አንድ ትልቅ የፖሊሲ ስትራቴጂ ወስዶታል። ለዚሁ ተግባር ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ እና በተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሕፃናት የትምህርት ቤት የመግባ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ያለ ጭንቀት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሰፊ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

ይህ መሠረታዊ ተግባር ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዲቆዩ በማድረግ የትምህርት ማቋረጥ ምጣኔን በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆችም ልጆቻቸውን በልበ ሙሉነት ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ በማድረግ የትውልድ ብክነትን የታደገ ትልቅ የኢንቨስትመንት መስክ ነው።

መንግሥት በትምህርት ዘርፉ የጀመረውን ሁለንተናዊ ሪፎርም በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል፣ በ2019 የትምህርት ዘመን በ727 ወረዳዎች 1 ሺህ 452 አዳዲስ የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት አቅዷል።

ይህ ግንባታ ከ87 ሺህ በላይ አዳዲስ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ገበታ የሚያስገባና የነገዋን ኢትዮጵያ በዕውቀት የሚረከብ ትውልድ ለማፍራት የሚደረግ ትልቅ መዋዕለ-ንዋይ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን የላቦራቶሪና የቤተ-መጽሐፍት ግንባታዎች፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሕፃናት ማቆያና የፈጠራ ማእከላት መቋቋማቸው፣ ለተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎችና ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን ፈጥሯል።

በድምሩ መንግሥት በትምህርት ዘርፉ እያደረገ ያለው ይህ ስትራቴጂካዊ ሪፎርም የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን ለማድረግ በሰው ኃይል ልማት ላይ የተተከለ ጽኑ መሠረት ሆኖ ይቀጥላል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት