አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለእኛ፤ በምናብ የምትሳል ህልም ብቻ ሳትሆን በተግባር የምትገነባ እውነታ ናት አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት አዲሱ አራዳ ፓርክ በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ አራዳ ፓርክ አዲስ አበባን ለመለወጥ ያለንን ርዕይ በተግባር ያሳየንበት አንዱ ስራችን ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል ተዘንግቶና ለአደጋ ተጋልጦ የነበረው የአራዳ አካባቢ፣ ዛሬ ተመልሶ ተገንብቶ አስደናቂ የከተማ አካል መሆን እንደቻለም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለእኛ፤ በምናብ የምትሳል ህልም ብቻ ሳትሆን በተግባር የምትገነባ እውነታ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጤናማ፣ ጽኑ፣ ለመጪው ትውልድ ተስፋን ከተጨባጭ ሀብት ጋር የምትሰጥ፣ በአፍሪካ መሪ፣ በዓለም መድረክ ደግሞ ተወዳዳሪ የሆነች ሀገር እየገነባን እንገኛለን ሲሉ አመልክተዋል።
አክለውም በየቀኑ ይህንን ተስፋ ወደ እውነታ የመለወጥ ተግባራችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት።