ቴክ

የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓት ቴክኖሎጂ ተመረቀ

By Adimasu Aragawu

May 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር ያለማውን የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓት ቴክኖሎጂን በይፋ አስመርቋል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ በዚህ ወቅት፥ አዲሱ የዲጂታል ሥርዓት ሀሰተኛ መረጃዎችን እና ሕግን የተላለፉ ስርጭቶችን ለመቆጣጠር ያግዛል ብለዋል።

ተመዝግበው እና ከባለስልጣኑ ፈቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃንን ዲጂታል በሆነ አግባብ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።

ቴክኖሎጂው የዜጎች ተሳትፎን ይበልጥ የሚያረጋግጥ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ሀሰተኛ መረጃዎችን እና ሕግን የተላለፉ ስርጭቶችን በመቆጣጠር የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን ገልጸዋል።

ይህም ዘርፉን በዲጂታሉ አውድ በመቃኘት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ተቋሙ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሁሉም የሚለውን መርህ በማንገብ ዲጂታላይዝድ የሆነች ሀገርን ዕውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዛሬ በይፋ የተመረቀው የቴክኖሎጂ ሥርዓትም ዘመኑን የዋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

በመቅደስ የኔሁን