አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት መስኮች አርአያ የሚሆን ለውጥ እያመጣች ነው አሉ የዩጋንዳ የዲያስፖራ ጉዳዮች ፕሬዚዳንት መሐመድ ባጎንዛ።
የዲያስፖራ ጉዳዮች ፕሬዝዳንቱ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማሻሻያዎችን በማካሄድ ረገድ ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
የአፍሪካ መዲና እና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ በሪፎርም ስራዎች ከአህጉሪቱ ግንባር ቀደም ናት ብለዋል።
በዚህም በኢኮኖሚ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት መስኮችም አርአያ የሚሆን ለውጥ እያመጣች እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህም አህጉራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና የአፍሪካን የጋራ አጀንዳ ለማራመድ ትልቅ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እጅግ አስደናቂ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በሥራው መደነቃቸውንም ተናግረዋል።
በአፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ ተብለው የማይጠበቁ ብሎም በአውሮፓ እና በአሜሪካ ደረጃ የሚገኙ የተዋቡ መንገዶችና ሆቴሎች መገንባታቸው የሀገሪቱ የሪፎርም ስትራቴጂ ውጤታማነት የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለሀገር እና ለአህጉር እድገት ቅድሚያ መስጠቷ ለተመዘገቡ ስኬቶች ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
ይህ አይነቱ አቅጣጫ አፍሪካውያን አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ እንዲራመዱ የሚያስችል ጠንካራ ስትራቴጂ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የአፍሪካ ዳያስፖራ ባለድርሻ አካላት መድረክ “የዳያስፖራ አቅም ለአህጉራዊ እድገት መጠቀምና ልምድ ልውውጥ” በሚል መሪ ሐሳብ በትናንትናው ዕለት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መካሄዱ ይታወቃል።
በዮናስ ጌትነት