የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት ሀገራዊ ብልፅግናን የሚያፋጥኑ መዋቅራዊ ለውጦችን በስኬት እያከናወነ ይገኛል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Adimasu Aragawu

May 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ዘላቂ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር ሀገራዊ ብልፅግናን የሚያፋጥኑ መዋቅራዊ ለውጦችን በስኬት እያከናወነ ይገኛል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ÷ መንግሥት የ’ዲጂታል ኢትዮጵያ’ን መነሻ ያደረገውና ግልጽነትን ያሰፈነው ዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት በተግባር ፍሬ እያፈራ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ሽግግር ነው ብሏል።

በተለይም የቴሌኮም ዘርፍ ሊበራላይዜሽን ርምጃዎች የውድድር መንፈስን በመፍጠር የኢንተርኔትና የዲጂታል ትስስር ተደራሽነትን በከፍተኛ ፍጥነት ማሳደግ መቻሉን አመልክቷል።

ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህን ለማስፈን ወሳኝ የሆነው የ”ፋይዳ” ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትም በተሳካ ሁኔታ በመተግበር ላይ ይገኛልም ነው ያለው።

ይህ ሥርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ የፋይናንስ አካታችነትን ከማረጋገጡም በላይ የመንግሥትን ሀብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማከፋፈል እና ድጋፍ ለሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ የላቀ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ዳግማዊ ሕዳሴያችን ነው ሲልም አብራርቷል።

የዜጎችን እንግልት ለማስቀረት እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል አማራጭ የማሸጋገሩ ጥረት ሌላው ተጨባጭ ስኬት የተመዘገበበት መስክ ነው ያለው መግለጫው÷ የተለያዩ የሚኒስቴሮች የፌዴራል ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በኤሌክትሮኒክስ መንገዶች መስጠት በመጀመራቸው የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ተደርጓል ብሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመንግሥት ክፍያዎችን በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች እንዲፈጸሙ መደረጉ የምዝበራና የሙስና ቀዳዳዎችን በመዝጋት፣ የመንግሥትን ገቢ በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ እና ሀብትን ለልማት ስራዎች ለማዋል አስቻይ ዐውድ መፍጠር አስችሏል።

ለዚህ የዲጂታል ሽግግር የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋነኛ ምሰሶ ሲሆን÷ ዘርፉ በተለይም ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድቷል።

በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች (ስታርትአፖች) ምቹ ምህዳር ከመፍጠር አኳያ የሕግ ማዕቀፎች መሻሻላቸው እና የፋይናንስ አቅርቦት አማራጮች መስፋፋታቸው ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል እንድትሆን ጠንካራ መሰረት ጥሏልም ነው ያለው አገልግሎቱ በመግለጫው።

መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ትኩረት ስቦ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ አበረታች ውጤቶች እያስመዘገበ ቀጥሏል ሲልም አመልክቷል።