የሀገር ውስጥ ዜና

የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ አዲስ ኢንዱስትሪያዊ የሥራ ባህል እየገነባ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Abiy Getahun

May 03, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከቴክኒካዊ ብቃት ባሻገር አዲስ ኢንዱስትሪያዊ ሰብዕና እና የሥራ ባህል እየገነባ ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

አገልግሎቱ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ አስመልክቶ ባወጣው መረጃ፤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ዓለም አቀፍ የጥራት ቁጥጥር ስታንዳርዶችን፣ ጥብቅ የጊዜ አጠቃቀምንና ስልታዊ የአመራር ክህሎትን በመላበስ ላይ ናቸው ብሏል።

ከታችኛው የሥራ እርከን ተነስተው በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ እስከ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት ደረጃ የደረሱ ወጣቶች፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው “ምርጥ ምርት” የሰው ሀብቷ መሆኑን እያስመሰከሩ ነው ሲልም ገልጿል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ‘በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምርትን ከማሳደግና የውጭ ምንዛሬን ከመታደግ ባሻገር ዕውቀትንና ክህሎትን ለዓለም የምናበረክትበት አዲስ የኢንዱስትሪ ምዕራፍ ተጀምሯል!’ በሚል ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ፤ 830 ፋብሪካዎችን ዳግም ወደ ስራ በማስገባት፣ 4.85 ቢሊየን ዶላር ገቢ ምርትን በመተካት እና 433 ሚሊየን ዶላር ከኤክስፖርት በማስገኘት አስደናቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር ውጤት አስመዝግቧል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ ሲጀምር፣ ግቡ ምርትን ማሳደግና የውጭ ምንዛሬን መታደግ ብቻ አልነበረም።

ከእነዚህ ኢኮኖሚያዊ ስሌቶች ባሻገር፣ ትልቁና ስትራቴጂካዊው ስኬታችን የተመዘገበው ኢትዮጵያን የዕውቀትና የክህሎት ምንጭ በሚያደርገው የሰው ሀብት ልማት ላይ ነው። ዛሬ ላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የፋብሪካዎች ስብስብ መሆኑ ቀርቶ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚገነቡ ብቁ ባለሙያዎችና መሪዎች የሚፈሩበት ታላቅ የተግባር ትምህርት ቤት መሆን ችሏል። ይህ ሽግግር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ ቴክኖሎጂ ላኪነትና ክህሎት አቅራቢነት ከፍ የሚያደርግ ለነገዋ ኢትዮጵያዊ መሠረት የሚጥል የታሪካችን እጥፋት ነው።

በታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በግዙፍ ፋብሪካዎች ውስጥ የታየው ተጨባጭ ለውጥ የመንግሥትን የፖሊሲ ጥንካሬ በተግባር የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ክፍያ በሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ብቻ ይተዳደሩ የነበሩ ውስብስብ የቴክኖሎጂ ሲስተሞች፣ ዘመናዊ የምርት መስመሮችና የሶፍትዌር መሠረተ-ልማቶች ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ወጣት መሐንዲሶችና ቴክኒሻኖች እየተመሩ ይገኛሉ። ይህ ስኬታማ የዕውቀት ሽግግር፣ መንግሥት ጥራት ያለው ፖሊሲ የመቅረጽ ብቻ ሳይሆን ፖሊሲን በተጨባጭ ወደ ተግባር የመለወጥና የማስፈጸም አቅም እንዳለው ትልቅ ማሳያ ነው።

በዘረፉ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም የተፈጠረላቸውን ምቹ ዐውድ ተጠቀመው ቴክኖሎጂን የመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ የመግራትና የማላመድ ብቃታቸውን በተግባር በማሳየት፣ ሀገራችን ለዘመናት የነበረባትን የቴክኖሎጂ ጥገኝነት በፈጠራ አቅማቸው እያስቀሩና አዳዲስ የሥራ ባሕልና የታሪክ ምዕራፍ እየጻፉ ይገኛሉ።

የ “ኢትዮጵያ ታምርት”ንቅናቄ ከቴክኒካዊ ብቃት ባሻገር፣ አዲስ ኢንዱስትሪያዊ ሰብዕና እና የሥራ ባህል እየገነባ ነው ። በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ዓለም አቀፍ የጥራት ቁጥጥር ስታንዳርዶችን፣ ጥብቅ የጊዜ አጠቃቀምንና ስልታዊ የአመራር ክህሎትን በመላበስ ላይ ናቸው። ከታችኛው የሥራ እርከን ተነስተው በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ እስከ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት ደረጃ የደረሱ ወጣቶቻች፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው “ምርጥ ምርት” የሰው ሀብቷ መሆኑን እያስመሰከሩ ነው።

መንግሥት የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ትክክለኛ ፍሬ የሚለካው በወጪ ንግድ ስሌቶች ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ የደረጀና በዕውቀት የበለጸገ አምራች ዜጋ መፈጠሩ ነው። በመሆኑም ይህን የክህሎት አብዮት ይበልጥ በማፋጠንና ዘርፉን የቴክኖሎጂ ምንጭ በማድረግ፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች በቁርጠኝነት ይቀጥላሉ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት