የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጪ ንግድ 10 ቢሊየን ዶላር ገቢ እናሳካለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

May 03, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጪ ንግድ 10 ቢሊየን ዶላር ገቢ ታሳካለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የአምራች ዘርፍ ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክረውን 4ኛውን ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ከ3 ቢሊየን ዶላር ተሻግሮ እንደማያውቅ አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጪ ንግድ 10 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማሳካት ትልቅ ድል እንደሚመዘገብ ገልጸው፥ የዚህ ድል መሰረቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር 4 ነጥብ 7 በመቶ የነበረው የአምራች ዘርፉ እድገት በዚህ ዓመት ወደ 10 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ማለቱን ነው የገለጹት፡፡

ይህ እድገት የተመዘገበው ንቅናቄው በወጪ ንግድ እንዲሁም በተኪ ምርት ባመጣው ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ባለፉት አራት ዓመታት 14 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርቶችን ማምረት የተቻለ ሲሆን፥ ይህ መጠን በቀጣይ አራት ዓመታት በእጥፍ እንደሚያድግ ጥርጥር የለውም ብለዋል፡፡

እነዚህን ተኪ ምርቶች በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ባንችል በልጆቻችን ላይ የእዳ ቀንበርን ከማጠናከርና ኢኮኖሚያችንን ከማዛባት አንድንም ነበር ነው ያሉት፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በተለያየ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ 993 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅሰው፥ ይህም በስራ እድል ፈጠራ፣ በተኪ ምርትና በወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ 3680 አዳዲስ ባለሃብቶችን መሳብ ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ብዙ ሺህ አልሚዎችን መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ኃይለማርያም ተገኝ