አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማምረት ክብራችንን፣ ነጻነታችንን እና ተጨማሪ እድገታችንን ማፋጠን እንችላለን አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የአምራች ዘርፍ ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክረውን 4ኛውን ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ አስደናቂ በሆነ መልኩ በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት እያሳየች ነው፡፡
አምራቾች የኢኮኖሚ አርበኛ ለመሆን ግብር መክፈል ብቻ ሳይሆን ኮንትሮባንድ እና ሌብነት መከላከል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
አምራቾች ካላመረታችሁ ወታደር ደመወዝ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በኢትዮጵያ የሚታየው ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ እንደማይኖርም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተመረቱ ካሉ ምርቶች በተጨማሪ ልናመርታቸው የምንችላቸውና የሚገቡ 96 ገደማ የምርት አይነቶች ተለይተዋል ነው ያሉት፡፡
እነዚህን ዘርፎች በፍጥነት በመተካት ከውጭ የምናመጣቸውን ምርቶች ማስቀረት ይኖርብናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሴራሚክስ ፍብሪካ እንደሚመረቅ ጠቁመው፥ የሚመረቁት ፋብሪካዎች የኢትዮጵያን ፍላጎት መቶ በመቶ ይመልሳሉ ነው ያሉት፡፡
በማምረት ክብራችንን፣ ነጻነታችንን እና ተጨማሪ እድገታችንን ማፋጠን እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጋራ በመስራትና ከጉድለቶቻችን በመማር የኢትዮጵያን ብልጽግና በጋራ እናረጋግጥ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢንዱስትሪና ማምረት ለብልጽግና፣ ለክብርና ለነጻነት ወሳኝ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ