አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለዘለቂ የቱሪዝም ልማት አስቻይ ፕሮጀክቶችን እየገነባች ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
በባህርዳር ከተማ የጣና ሐይቅ ዙሪያ የሚገኘውን የቀድሞው ጣና ሆቴል ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ‘ፎር ፒ ቢ ኤስ’ በሚል ስያሜ ለመገንባት በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ግንባታ ተጀምሯል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባታውን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፥ በባህር ዳር እየተገነቡ ያሉ ሪዞርቶችና ሆቴሎች ከተማዋን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡
የሆቴል ኢንቨስትመንትን በማስፋት የቱሪዝም ሀብትን ማሳደግ በልዩ የመፈጸም ብቃት እየተከናወነ ያለ ተግባር መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም የለውጡ መንግስት ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መጀመርና መፈጸምን ባህል ለማድረጉ ባህር ዳር ምስክር ናት ብለዋል።
በመደመር እሳቤ ለዘላቂ ቱሪዝም እየተሰራ ያለው ስራ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጥና መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆቴሉ በ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ በ32 ሺህ 440 ስኩዌር ሜትር ላይ የሚገነባ ሲሆን፥ 4 ዘመናዊ ሬስቶራንቶች፣ ሱቆች፣ 120 ዘመናዊ የመኝታ ክፍሎች፣ የመዋኛ ገንዳዎችና ዘመናዊ የሁነት ማከናወኛዎችን ያካተተ ነው፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዚህ በፊት በግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ያስመሰከረውን የአፈጻጸም ብቃት በዚህ ፕሮጀክትም ሊያሳይ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በለይኩን ዓለም