የሀገር ውስጥ ዜና

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደቡብ ሱዳን በቤት ግንባታ ዘርፍ ለመሰማራት ተስማማ

By Yonas Getnet

May 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደቡብ ሱዳን በቤት ግንባታ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በጁባ ከተማ በቤቶች ልማትና አስተዳደር ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችለው ይህ ስምምነት በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) እና በማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ግዛት መንግሥት አስተዳደሪ ኢማኑኤል አዲል ተፈርሟል።

ረሻድ ከማል (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ኮርፖሬሽኑ በምሥራቅ አፍሪካና በመላ አህጉሪቱ በዘርፉ የመሪነት ደረጃን በመውሰድ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማስገኘት እየሰራ ይገኛል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ግዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውና አዋጭ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢማኑኤል አዲል በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እና ፈጣን የከተሞች እድገት ለመላው አፍሪካውያን ተምሳሌት እየሆነ መምጣቱን አውስተዋል።

በተለይም በቤት ልማት ዘርፍ በኢትዮጵያ ያለውን ተሞክሮ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመሆን በጁባ ከተማና በግዛቱ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ