የሀገር ውስጥ ዜና

የዛሬው አርበኝነት ሀገርን ከድህነትና ኋላቀርነት ማላቀቅ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Mikias Ayele

May 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነቸ አቤቤ የዛሬው አርበኝነት ሀገርን ከድህነት፣ ኋላቀርነት እና ተመጽዋችነት ማላቀቅ ነው አሉ፡፡

ከንቲባዋ 85ኛውን የአርበኞች ቀን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ቀኑን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን እና ጀግኖች አርበኞች በተገኙበት ማክበራቸውን ገልፀዋል፡፡

አባቶቻችን እና እናቶቻችን ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት፣ ዛሬ በነጻ ሕዝቦች ፊት በኩራት የምትጠራዋን ሉዓላዊት ሀገራችን ኢትዮጵያን አቆይተውልናል ብለዋል።

ይህን ዘመን ተሻጋሪ እውነት እና ምትክ የማይገኝለት የታሪክ መስዋዕትነት ትውልድ ፈጽሞ እንደማይዘነጋው ጠቅሰው÷ የዛሬው ዘመን ትውልድ የአባቶቹን መታወሻ እና የታሪክ ቅርስ ከመዘከርና ከመጠበቅ ባሻገር አዲስ የአርበኝነት አውድ ሊፈጥር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የትናንቱ አርበኝነት ሀገርን ከወራሪ ማዳን እንደነበረ ጠቅሰው፤ የዛሬው አርበኝነት ሀገርን ከድህነት፣ ከኋላቀርነት እና ከተመጽዋችነት ማላቀቅ ነው ብለዋል።

ጀግኖች አባቶቻችን ወራሪውንም ሆነ የውስጥ ባንዳውን ታግለው አሸንፈው ሀገር አቆይተውልናል ነው ያሉት።

እኛም ዛሬ የልማት እና የሰላም ጉዟችንን ለማደናቀፍ የሚሞክሩትን የዘመኑን ባንዳዎች በአንድነት፣ በንቃት እና በሥራ ማሸነፍ ግድ ይለናል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።