ፋና ስብስብ

የአርበኞች ተጋድሎ …

By Adimasu Aragawu

May 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም የወረረበትና ከጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጋር ለ5 ዓመት ታግሎ የተሸነፈችበት 85ኛ ዓመት የአርበኞች በዓል ዛሬ እየተከበረ ነው።

ፋሽስት ጣሊያን በዓድዋ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ዳግም ኢትዮጵያን የወረረበትና ኢትዮጵያውያን አርበኞች ሕዝቡን በማስተባበር ከአምስት ዓመት ተጋድሎ በኋላ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ድጋሚ ድል አድርገዋል፡፡

የአርበኞች ቀን ሲከበር የአሁኑ ትውልድ የአርበኞችን የድል ታሪክ በተለያዩ ዘርፎች ውጤት በማስመዝገብ እንዲሁም የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ሊደግመው ይገባል፡፡

ከዓድዋ ድል ማግስት ኢትዮጵያ የግዛት ማስፋፋት ልታስብ ትችላለች በሚል የብዙ ቅኝ ገዥ ሀገራትን ትኩረት ስባ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

በሰሜንና በደቡብ ምስራቅ ጣሊያን፣ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ እንዲሁም በምስራቅ ፈረንሳይ እንደከበባ ያለ አካሄድ ቃጥቷቸው ነበር፡፡

የድንበር የውል ስምምነቶችን ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት መሞከር ጣሊያን ለረጅም ጊዜ የሰራችው ኢትዮጵያን የመያዣና ለበቀል የሚሆን ጊዜ የማመቻቻ ስራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ለዚህ አብነት የሚሆነው ጣሊያን በቅኝ በያዘቻት የጣሊያን ሶማሌላንድ እና በኢትዮጵያ መንግሥት በ1900 ዓ.ም የተደረገው ስምምነት ነው፡፡

ፋሽስት ጣሊያን በዓድዋ የገጠመውን የሽንፈት ቁስል በድል ለመሻር ጣሊያንን ለመምራት ወደ ስልጣን የመጡት ሁሉ እያሰቡ እየተመኙ ዓመታት ቢያልፉም በ1922 ወደ ስልጣን የመጣው ሞሶሎኒ ተንኮል በመፈለግ እረፍት እንዳልነበረው ይጠቀሳል፡፡

በሐረር የኦጋዴን አውራጃ የወልወል ወረራም በዚሁ ስሜት የተወለደ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል።

በሕዳር ወር 1927 ዓ.ም ለወልወል ግጭት በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገ የድንበር ስምምነት ስምምነቱን ለማስተግበር ወደ ስፍራው የሄዱ ኮሚሽነሮች ቦታው ላይ ሲደርሱ የጣሊያን ወታደሮች ቀድመው የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በማግኘታቸው ለቀናት በፍጥጫ ከቆዩ በኋላ ወደ ጦርነት አምርተዋል፡፡

ወልወል የኢትዮጵያ ይዞታ ብትሆንም በመንግሥቱ የጥበቃ መዳከም ተጠቅማ የሰፈረው ፋሽስት ጣሊያን በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ቀጥሎ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የተፈጠረው መካረርም ወደ ጦር መማዘዝ እንዲያድግና የዓድዋን የሽንፈት ካባ አውልቆ ኢትዮጵያን ድል በመንሳት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያጣውን ክብር ለመመለስ አጋጣሚውን እንደመንደርደሪያም ተጠቅሞበታል፡፡

ከሮም የተላከው የጣሊያን ጦር መስከረም 22 ቀን 1928 የመረብን ወንዝ ተሻግሮ በዓድዋ፣ በዓዲግራት ጦርነት ከፍቶ ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን አርበኞችና መሪዎችም ዓለም የፋሽስት ጣሊያን ወራሪነትን እንዲያይና በከበባ ትጥቁን እንዲሁም ስንቁን ለማስጨረስ በማሰብ ጦሩ ምንም አይነት ችግር ሳይገጥመው ወደ መሀል ሀገር እንዲገባ ፈቀዱ፡፡

በ9 ክፍለ ጦሮች ተዘጋጅቶ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የጣሊያን ጦር ቤታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ እርሻቸውን ሁሉ ትተው ጫካ በገቡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች እረፍት እያጣም ቢሆን ለአምስት ዓመታት ቆይታ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያውያን የመንፈስና የአካል ጉዳት አቅም ሊያሳጣቸው ቢሞክርም ጠላትን እምቢ በማለት ዓድዋ ላይ ድል ያደረጉ አባቶችን ታሪክ በመድገም ከአምስት ዓመታት ትግል በኋላ ሀገራቸውን ከፋሽስት ነጻ አውጥተዋል፡፡

ፋሽስት ጣሊያን 40 ዓመታት ያህል ሲዘጋጅ ቆይቶ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ኢትዮጵያን የወረረ ቢሆንም የኢትዮጵያ አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት በድጋሚ ድል አድርገዋል።

ቀኑ የኢትዮጵያ አርበኞች በአንድነት በፋሽስት ጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት የከፈሉትን መስዋዕትነትና ያስገኙትን ድል ለማሰብ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይከበራል፡፡