የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ብሔራዊ አርበኞችን ይፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

May 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ብሔራዊ አርበኞችን ይፈልጋል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ለ85ኛው የአርበኞች በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው።

በመልዕክታቸውም የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ብሔራዊ አርበኞችን ይፈልጋል፤ የራስ ፍላጎትን፣ ባንዳነትን እና ወራሪን እምቢ የሚል አርበኝነት ብለዋል።

የኢንዱስትሪ አርበኞች፣ የግብርና አርበኞች፣ የጸጥታ አርበኞች፣ የፖለቲካ አርበኞች፣ የንግድ አርበኞች፣ የዲፕሎማሲ አርበኞች፣ የመንግሥት አገልጋይ አርበኞች፣ የሕክምና አርበኞች እንዲሁም የትምህርት አርበኞች እንደሚያስፈልጉም አብራርተዋል።

ይሄንን በዓል የምናከብረው የየራሳችንን የአርበኝነት ደረጃ በመገምገም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለኢትዮጵያ ምን ያህል አርበኞች ነን? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ዛሬም የግል ፍላጎት የሚያሸንፋቸው ደካሞች አሉ፤ ሀገርን አፍርሰው የግል ቤት መሥራት የሚመኙ በማለት ጠቅሰው÷ ትልቁን መርከብ አፍርሰው ትንንሽ ታንኳዎችን ለመሸጥ የሚመኙ እንዲሁም ለቅንጥብጣቢ ነገር ውርደትን ለመሸከም የማይሳቀቁ ሲሉም አብራርተዋል።

ዛሬም ወራሪዎች አሉ፤ በአካል ሀገርን ለመውረር ካሰፈሰፉት በተጨማሪ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ሌብነት የሚባሉ እንደ ሰርዶ ሀገርን ወርረው ሽባ የሚያደርጉ ጠላቶች አሉ ብለዋል።

ሀገርን ለባዳ ከሚሸጡት ባንዳዎች እኩል የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሚሸጡ እንዲሁም አገልግሎትንና የሕዝብን ሀብት የሚሸቅጡ ባንዳዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል።

ብሔራዊ አርበኝነት ማለት እነዚህን ሦስት ጠላቶች ታግሎ ማሸነፍ ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ዛሬ የምናየውን የኢትዮጵያ ለውጥና ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለው ብሔራዊ አርበኞች በየአካባቢው በመኖራቸው ነው ብለዋል።

ብሔራዊ አርበኞች ሦስቱን ጠላቶች እያሸነፉ ቢሆንም ገና ሙሉ በሙሉ ድልን አልተቀዳጁም በማለት ገልጸው÷ ድሉ እንደ ሚያዚያ 27 የሚታወጀው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሁም በዓለም ደረጃ ከሚገኙ ኃያል ሀገራት አንዷ ስትሆን ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ይሄንን ድል እውን ለማድረግ ኢትዮጵያን የሚወዱ የኢትዮጵያ አርበኞች ሁሉ እንዲነሡ ጥሪ አቅርበዋል።