አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አርበኝነት መልከ ብዙ፤ ቀለመ ደማቅ ነው። አርበኞች በቀደመው ዘመን ለሀገር በአንድነት በመቆም በከፈሉት መሰዋዕትነት ሀገር በክብር ኖራለች፡፡
ነገር ግን አርበኝነት መገለጫው እንደዘመኑ እና እንደሁኔታው ይለያያል። አርበኝነት ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል በዱር በገደል መዋደቅ፣ በረሃ መውረድ፣ ጫካ መላመድ እና በጀግንነት ከጠላት ጋር በጦር መሳሪያ መፋለም ብቻ አይደለም።
ይልቁንስ ስለሕዝብ እና ስለሀገር ጥቅም ብልሹ ሥርዓትን በድፍረት የሚሞግት፣ ስልታዊ በሆነ የፖለቲካ ጥበብ ሕዝብን የሚያነቃ፣ ለግል ጥቅም እና ዝና ሀገሩን ያልበደለ፣ በጥበብ ሥራ እንከኖችን የነቀፈ፣ ሀገር በምትፈልገው ጊዜ እና ቦታ ሁሉ የተጋ አርበኛ ነው።
የሀገር ብልጽግና እንዲሳካ፣ አንድነት እንዲጠነክር፣ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ነጻነት እና እኩልነት እንዲሰፍን የራስ ፍላጎትን የማያስቀድሙ፣ ባንዳነትን እና ወራሪን እምቢ የሚሉ በየመስኩ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ያስፈልጋሉ።
ከእነዚህ መስኮች መካከል አንዱ የሆነው ጥበብ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የጎላ ሚና ይጫወታል። የሰዎችን አስተሳሰብና አመለካከት በመቅረጽ፣ ሀገርን ከመበታተን አደጋ የሚከላከልና የጋራ ራዕይን የሚያቀጣጥል ኃይል ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
ብሔራዊ ስምምነትና የሀገር ፍቅር ስሜት በጥልቅ ስሜታዊ ትስስር ላይ የሚመሠረት በመሆኑ ጥበብ የጋራ ብሔራዊ ምልክቶችን፣ ዜማዎችንና መግባቢያዎችን በመፍጠር ሕዝቡ ተመሳሳይ ነገር እንዲሰማውና ተመሳሳይ የወደፊት ታላቅነትን እንዲያልም ያደርጋል። ጥበብ ሀገር ይሰራል የሚባለውም ከዚህ አንጻር ነው።
ኢትዮጵያ ዘመናትን ባስቆጠረው ታሪኳ ቁመቷን ቆራርጠው ወርዷን ሸርሽረው መሃሏን ሊያፈራርሱ የሚሹ ብዙዎች ቢነሱም የቁርጥ ቀን ልጆቿ ሃሳብን በሃሳብ፣ ጥላቻን በፍቅር፣ ኃይልን በመግባባት አለፍ ሲልም እንደአመጣጡ እያስተናገዱ ሀገርን ከባህሏ፣ ማንነቷ እና ክብሯ ጋር ማስቀጠል የሚችሉ ልጆችን ያፈራች ማህጸነ ለምለም ናት።
በኪነ ጥበቡ ዘርፍም ለሀገራቸው ሰላም፣ ለኢትዮጵያዊነት ግንባታ፣ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ለወንድማማችነትና እህትማማችነት፣ ለፍትሃዊነት፣ ለነፃነትና እኩልነት ጥበብን በአግባቡ የተጠቀሙ የጥበብ ሰዎችን አፍርታለች።
የሀገር ባለውለታ ለሆኑና በጥበብ ሙያቸው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ የኪነጥበብ ሰዎች በመዲናዋ አዲስ አበባ የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል።
ሀገሪቱ ታሪክ አትረሳም ውለታ አትዘነጋምና የሀገር ባለውለታዎች የሆኑ ታላላቅ ጠቢባን አርበኞችን የመታሰቢያ ሐውልት በማቆም ዘክራቸዋለች።
መታሰቢያ ሐውልት ከቆመላቸው የሀገር ባለውለታ የጥበብ ሰዎች መካከል በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ታላቁ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ይገኝበታል።
ስለሀገር፣ ስለፍቅር፣ ስለጀግንነት፣ ስለፖለቲካ፣ ስለተፈጠሮ እንዲሁም ስለውበት ጥልቅ እና ልብ የሚነኩ ሥራዎችን ለሀገር አበርክቷል።
ጥላሁን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ላደረገው አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ያገኘ ሲሆን÷ ህይወቱን በሙሉ ለሙዚቃ በማበርከቱ ከኢትዮጵያ ኪነጥበብና የብዙኃን መገናኛ ሽልማት ድርጅት “የሙሉ ዘመን” ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
ሰንደቅ ዓላማና የሀገር ፍቅር ስሜት በአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ልብ የጸናች ናትና ሙዚቃዎቹ የሀገር ፍቅር የወለዳቸው፣ ለተገፉትና ለተበደሉት የሰው ልጆች ነፃነት ጠያቂ ሆነው ይደመጣሉ።
ሌላኛው የሀገር ባለውለታ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያሳረፈው ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ላበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦ ህያው ምስክር ይሆን ዘንድ ሐውልት ቆሞለታል።
ትኩሳት፣ ሌሊቱ ካለቀ በኋላ፣ አምስት ስድስት ሰባት፣ ቦርጭቃ እና “እነሆ ጀግና” ያሉ ሥራዎቹ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ስማቸው በጉልህ የሚጠቀሱ የጥበብ ሥራዎቹ ሲሆን÷ በአጫጭር ታሪኮቹና በጋዜጣዊ ዓምዶቹ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው።
ግጥም እና ተውኔት ሲጽፍ የልቡን ቀለም እየቀባ ያቀርባል የሚባልለት ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ስለሕዝብ፣ ስለሀገር፣ ስለወንዝ፣ ስለስልጣኔ፣ በአጠቃላይ ያመነበትን እውነት በቅኔ ወደ ብርሃን ያወጣል።
ሎሬት ፀጋዬ በርካታ ግጥሞችን፣ የቴአትር ሥራዎችን የተለያዩ መጣጥፎችንና ዘፈኖችን ለሀገር አበርክቷል። ታላቁ ባለቅኔና የተውኔት አዘጋጅ ዘመን ተሻጋሪ የሆነችው “ጴጥሮስ ያችን ሰዓት” የተሰኘችው ግጥም የብዙዎች አዕምሮ ውስጥ የታተመች ናት ሊባል ይችላል።
የዓለም ባለ ቅኔዎች 15ኛ ጉባኤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን በሀገሩ ቋንቋና በእንግሊዝኛም ጭምር ያበረከታቸውን ግጥሞች፣ ቅኔዎች እና ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን በመመርመር ሥራዎቹ የሰው ልጅን እኩልነት፣ ነፃነት፣ ወንድማማችነትና ፍቅር አበክረው የገለጹ መሆናቸውን ተረድቶ ባለ ቅኔ ሎሬት የሚያገኘውንና የተከበረውን ባለ ወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል ሸልሞታል።
ይህ ታላቅ የጥበብ ሰው ለሀገር በብዙ የተጋ የጥበብ ሰው ነውና በትውልድ ሲዘከር ይኖር ዘንድ መታሰቢያ ሐውልት ቆሞለታል።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ ከሆኑ አንጋፋ ድምጻዊያን መካከል ክቡር ዶክተር ዓሊ ቢራ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ይመደባል።
በተለይም የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃዎች ከፍ ብለው እንዲደመጡና በርካታ ሰዎች ጋር ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር አሊ ቢራ የነበረው ሚና እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡ አፋን ኦሮሞ መናገር ለማይችሉ የሙዚቃ አፍቃሪዎች አርቲስት አሊ ቢራ ሙዚቃ ቋንቋ ነው የሚለውን ብሂልም በተግባር አሳይቷል። ለአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በኢትዮጵያ የጥበብ መድረክ ላይ ነግሶ የትውልድ ተምሳሌት ሆኖ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ ወሳኝ ድርሻ የተጫወተው ድንቅና አንጋፋ የጥበብ ባለሙያ አሊ ቢራ ከሀገር ውጪም አሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ሳንታ ሞኒካ ከሌጅ የሙዚቃ ትምህርት በመከታተል የጥበብ ዕውቀትና ክህሎቱን አሳድጎ በላቀ የሙያ ብቃት ሕዝብን ለማገልገል ያለውን ፍላጎት በተግባር አረጋግጧል።
አርቲስቱ ያልዘፈነበት የሕይወት ጉዳይ የለም። ፍቅርን፣ እርቅን፣ ሰላምና መተሳሰብን አጉልቶ አሳይቷል። አንድነትን ሰብኳልና ይህ ውለታው ለትውልድ መማሪያ ይሆን እና ይዘከር ዘንድ ሐውልት አቁማለታለች።
ሌላኛው አርቲስት ሐጫሉ ሑንዴሳ የግፍን ቀንበር ለመስበር በብዙ የታገለ፣ የነፃነት ድምፅ፣ ጭቆናን የሚጠየፍ፣ ጨቋኞችን የማይፈራ በብርቱም የሚታገል የትውልድ ድምፅ ነበር።
ሐጫሉ በሙዚቃ ሥራዎቹ የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፣ ማንነትና ጥያቄዎች በልዩ ጥበብ በማቅረብ ይታወቃል። ይህ ድንቅ አርቲስት የጥበብን ኃይል ለመብትና ለእኩልነት ትግል መሳሪያ በማድረግ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የማይፋቅ አሻራ ጥሏል።
ሙዚቃን እንደ ትግል መሣሪያ የተጠቀመና በመከራ ውስጥ አልፎ ለሕዝብ ድምፅ መሆን የቻለ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ አደባባይ ላይ የቆመው እና ለምረቃ የበቃው የአርቲስት ሐጫሉ ሐውልት ይህንን ውጣ ውረድ እና ጥናት የሚመሰክር ህያው ምስክር ነው።
በጥበብ ሥራቸውን በቋሚነት የሚመሰክር እና የታሪክ ማኅደር የሚሆን ሐውልት ከቆመላቸው የሀገር ባለውለታዎች መካከል ሌላኛው አርቲስት ድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ ነው።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታላቅ አምባሳደር የሆነው ድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ÷ ለሀገር አንድነትና ለሰላም በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
“ሰላም” የተሰኘው ሥራው የሀገር ፍቅርንና አንድነትን በማቀንቀን ረገድ በሕዝብ ዘንድ እንደ ብሔራዊ መዝሙር የሚታይ ተወዳጅነትን አግኝቷል።
እነዚህ ድምጻዊያን ያዜሙላት፣ ባለቅኔዎች የተቀኙላት፣ ደራሲዎች የናፈቋት እና የተመኟት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ሁሉም በየተሰማራበት መስክ በአርበኝነት ጠንክሮ መስራት ይጠበቃል።
ጥበብ ሀገር ትሠራለች፤ ሀገርም ጠቢብን ታከብራለችና የሀገር ባለውለታ የሆኑና በጥበብ ሙያቸው ለኢትዮጵያ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በአዲስ አበባ ከተማ የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል።
በብርሃኑ አበራ