አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክክር የሐሳብ ልዩነቶችን የመፍቻ ብቸኛ መንገድ መሆኑን እናምናለን አሉ ከትጥቅ ትግል የተመለሱ አካላት፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ቆይተው ከተመለሱ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ከዚህ በፊት በተደረገ ውይይት በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩና ሰላምን መርጠው የተመለሱ አካላት ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ 17 አጀንዳዎችን ሰንደው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
እነዚህ ወገኖች ቀደም ሲል በተደረገው ውይይት ያነሳችኋቸውን ጥያቄዎች ኮሚሽኑ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡንም ተናግረዋል።
መድረኩ ከትጥቅ ትግል የተመለሱ አካላት ከኮሚሽኑ ጋር ተቀራርበው ለሰላም የሚሰሩበት እና የቀሩ ወገኖችን ወደ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ምክረ ሐሳብ የሚያዙበት ይሆናል ብለዋል።
ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ በሌሎች አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለማካተት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የተሣታፊዎች ተወካዮች ባደረጉት ንግግር ጥያቄዎቻቸውን በኃይል ለማስመለስ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስታውሰው÷ የሰላም ጀግና መሆን እንደሚሻል አስረድተዋል፡፡
ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ውይይት 200 የሚደርሱ በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ የቆዩና አሁን ላይ ሰላምን መርጠው የተመለሱ ወገኖች እየተሳተፉ መሆናቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።