አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አርሰናል አትሌቲኮ ማድሪድን በማሸነፍ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ለአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ማለፉን አረጋግጧል፡፡
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በመድረኩ ለፍጻሜ ሲያልፍ የዘንድሮው ለ2ኛ ጊዜ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰው በ2005/6 የውድድር ዓመት ነበር፡፡
በፈረንጆቹ 2006 በፓሪስ በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ በባርሴሎና 2 ለ 1 ተሸንፈው ዋንጫውን የተነጠቁት መድፈኞቹ ያንን ታሪክ ለመቀልበስ ወደ ቡዳፔስት ያቀናሉ፡፡
በወቅቱ አርሰናል ለፍጻሜ ሲደርስ አንድም ሽንፈት ያላስተናገደ ሲሆን፥ በውድድሩ የፍጻሜውን ጨዋታ ጨምሮ 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡
መድፈኞቹ በጥሎ ማለፉ የመድረኩን ሀያል ክለብ ሪያል ማድሪድን፣ በሩብ ፍጻሜው ዩቬንቱስን እንዲሁም በግማሽ ፍጻሜው ቪያሪያልን በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡
በፓሪስ በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ጀርመናዊው ግብ ጠባቂ የንስ ሌማን በ18ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ መሰናበቱን ተከትሎ አርሰናል ከ70 ደቂቃ በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ለመቀጠል መገደዱ ይታወሳል፡፡
ሶል ካምቤል በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ባስቆጠራት ግብ መድፈኞቹ ጨዋታውን ሲመሩ ቢቆዩም፥ በ76ኛው እና 80ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠሩባቸው ግቦች ሽንፈት አስተናግደዋል፡፡
ባለፈው የውድድር ዓመት እስከ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ የቻለው የሰሜን ለንደኑ ክለብ በድምር ውጤት በፒኤስጂ ተሸንፎ ለፍጻሜው ሳያልፉ መቅረቱ የሚታወስ ነው፡፡
ዘንድሮ ከ20 ዓመታት በኋላ ለ2ኛ ጊዜ ወደ ትልቁ መድረክ ፍጻሜ ያለፉት መድፈኞቹ ከሦስት ሳምንታት በኋላ በሀንጋሪ ቡዳፔስት የፒኤስጂ እና ባየርን ሙኒክን አሸናፊ ይገጥማሉ፡፡
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ደጋፊዎች የቡዳፔስቱ የፍጻሜ ፍልሚያ የ2006ቱን የስታድ ደ ፍረንስ ቁጭት የሚወጡበት እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል፡፡
በተመሳሳይ በዚህ የውድድር ዓመትም በመድረኩ አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው አርሰናል በታሪኩ የመጀመሪያውን የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ለማሳካት ይፋለማል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ