ቢዝነስ

የአፍሪካን የዕዳ ጫና ለመከላከል አስቸኳይ እና የተቀናጀ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ቀረበ

By sosina alemayehu

May 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአፍሪካ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለውን የውጭ የዕዳ ጫና ስጋት ለመከላከል አስቸኳይ እና የተቀናጀ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቀረበ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው የአፍሪካ ሉዓላዊ የፋይናንስ ፎረም ላይ የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ እንዳሉት÷ የአፍሪካ ኢኮኖሚ በጠባብ የፋይናንስ አቅርቦት ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች በነገሱበትና እርግጠኝነት በጠፋበት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡

ይህ ዓለም አቀፋዊ ለውጥ ኢንቨስትመንት የፋይናንስ አቅምን በማጥበብ፣ ኢንቨስትመንትን በመቀነስ የፖሊሲ ምርጫዎችን በመገደብ እና የካፒታል ወጪን በማናር ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ አፍሪካ የምታስመዘግበው የኢኮኖሚ ዕድገት የ1 ነጥብ 2 ትሪሊየን ዶላር የውጭ ዕዳ ጫና ስጋት እንደተጋረጠበት ገልፀዋል፡፡

በአህጉሪቱ እየናረ የመጣው የዕዳ ጫና እና እየጠበበ ያለው የፋይናንስ አቅም የአፍሪካን የልማት ጉዞ እያደናቀፈ መሆኑን ገልጸው÷ ጫናውን ለመከላከል አስቸኳይና የተቀናጀ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተግዳሮቶች ቢኖሩም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጥንካሬ እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው÷ በ2025 የ3 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡና ይህም በሚቀጥሉት ዓመታት ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ቀውስ ውስጥ የሚገኙ ሰባት ሀገራትን ጨምሮ 16 የአፍሪካ ሀገራት ለከፍተኛ የዕዳ ስጋት የተጋለጡ ሲሆን፤ የአህጉሪቱ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል፡፡

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት የሚገመገሙበት መንገድ መዋቅራዊ ችግር ያለበት መሆኑን የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው፤ ሀገራቱ ከአቅማቸው በላይ የሆነ የብድር ወለድ እንዲከፍሉ እያደረጋቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ዘላቂነትን ማዕከል ያደረገ የዕዳ አስተዳደር ስትራቴጂ መቅረጽ፣ ተአማኒነት ያላቸው ተቋማዊና የመረጃ ስርዓቶችን መገንባት እንዲሁም የአፍሪካ የብድር ደረጃ መመዘኛ ኤጀንሲን ማቋቋም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመሳፍንት ብርሌ