የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም ያለችበትን ሁኔታ የምንሻገረው ስንሰራ ብቻ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

May 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዓለም ያለችበትን ሁኔታ የምንሻገረው ስንሰራ ብቻ ነው አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱልልታ ወረዳ በ2 ሺህ 150 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ማሳን ከጎበኙ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ÷ ከፍተኛ ውጤት የታየበት የበጋ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ ከፍተኛ አምራች እንድትሆን፣ በሴፍቲኔት የሚደገፉ ዜጎች ነጻ እንዲወጡ እና ገቢ እንዲያድግ ማድረጉን ገልጸዋል።

የበጋ ስንዴ ለኢትዮጵያ የማይናቅ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም በትክክል ባለመመራቱ ውጤቱ ዝቅተኛ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን ግን በየዓመቱ የሚታየው ለውጥ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተው፤ 330 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት ቀላል አይደለም ብለዋል።

በድፍን አፍሪካ በዚህ ደረጃ የሚያመርት ሀገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተገኘው ውጤት ሳንዘናጋ ስራችንን አጠናክረን ከቀጠልን እና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ከተጠቀምን በአጭር ጊዜ ውስጥ 500 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት እንችላለን ነው ያሉት፡፡

ግብርና ልክ እንደ ኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂ፣ ማዕድን እና ቱሪዝም ዘርፎች ራሱን ችሎ አመርቂ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከትናንትናው እያረምን እና እያሻሻልን ከሄድን የምናስባትን ሀገር ለመፍጠር መሰረት እንዳለ ያሳያል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ዓለም ያለችበትን ሁኔታ የምንሻገረው ስንሰራ ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ካረስን፣ የጀመርነውን ከጨረስን እንሻገራለን ከስራ ውጪ መሻገሪያ መንገድ የለም ብለዋል፡፡

ሁሉንም ወቅት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤ መጪው ክረምት ብዙ ስራ የሚጠበቅበት ወቅት በመሆኑ አርሶ አደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ