የሀገር ውስጥ ዜና

ለማክሮኢኮኖሚ መረጋጋት ወሳኝ ሚና ያለው የዕዳ አስተዳደር …

By Mikias Ayele

May 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍኤምሲ) የዕዳ አስተዳደር ከቴክኒካዊ ተግባር ባለፈ ለማክሮኢኮኖሚ መረጋጋት፣ ለልማት ስትራቴጂ እና ለፖሊሲ ተዓማኒነት ወሳኝ ሚና አለው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው የአፍሪካ ሉዓላዊ የፋይናንስ ፎረም ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት÷ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት በተደራራቢ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎች ምክንያት ለከፍተኛ የፋይናንስ ስጋት ተጋልጣለች።

በተለይም አህጉራዊ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከጠቅላላ ዕዳ አንጻር በፈረንጆቹ 2010 ከነበረበት 44 በመቶ በ2024 ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማለት ሀገራት ግዴታ የመወጣት አቅማቸውን እየፈተነው እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ተግዳሮት ለመወጣት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተገበረች መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን፣ የገንዘብ ፖሊሲ እና የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ መጠናከሩን፣ በዕዳ አስተዳደር ረገድ ግልጽነት መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡

በነዚህ የሪፎርም ርምጃዎች አማካኝነት የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ፣ የወጪ ንግድ እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት እያደገ እንዲሁም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በጠንካራ ሁኔታ እየቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በቡድን 20 ሀገራት የዕዳ ማዕቀፍ አማካኝነት ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ የዕዳ ሽግሽግ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል።

በመሳፍንት ብርሌ