የሀገር ውስጥ ዜና

የስንዴ በረከት ተምሳሌት…

By Abiy Getahun

May 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዘመናት በዓለም አቀፍ መድረክ ስሟ ከረሃብና ከድርቅ ጋር ይያያዝ የነበረችው ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ጠባሳዋን በመፋቅ ስሟን የቀየረ ትልልቅ ስኬት መቀዳጀት ጀምራለች፡፡

በአንድ ወቅት የርዳታ እህል ጠባቂ የነበረችው ሀገር ዛሬ ላይ በገዛ መሬቷና በልጆቿ ጥረት ስሟን በአዲስ የታሪክ ብዕር እየጻፈች ትገኛለች።

በተለይም በስንዴ ዘርፍ አስደናቂ ስኬቶች እየተመዘገቡ ሲሆን፥ ይህም በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን የመንግሥት ቁርጠኝነትና የኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ጠንካራ የሥራ ውጤት ነው፡፡

በስንዴ ምርት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የታየው ዕድገት ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል የያዘችውን ግብ ከቃላት አልፎ በተግባር ማሳየት ያስቻለ ነው፡፡

በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ ከመጠበቅ ይልቅ በመስኖ ልማት የተጀመረው ጉዞ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ እንዲቀየር አድርጓል።

በመስኖ የሚለማው መሬት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በአግባቡ በመጠቀም ለልማት ማዋል እንደጀመረች ትልቅ ማሳያ ሆኗል።

ከ2012 ዓ.ም ወዲህ የስንዴ ልማት በአማካይ የ39 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት እያስመዘገበ ሲሆን፥ በ2017 ዓ.ም የተመዘገበው የ280 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ሀገሪቱ በስንዴ ምርት የደረሰችበትን ደረጃ የሚያሳይ ነው።

ከዚህ ምርት ውስጥ 128 ሚሊየን ኩንታል ያህሉ በመስኖ ልማት የተገኘ ሲሆን፥ የቀድሞውን ታሪክ የሚቀይርና ኢትዮጵያ በማንኛውም ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ማምረት እንደምትችል ለዓለም ያሳየችበት ድል ነው።

በመስኖ ልማት በ2022 ዓ.ም ለማሳካት ታቅዶ የነበረውን 128 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ምርት ከ5 ዓመታት ቀደም ብሎ በመሳካቱ ዕቅዱ በድጋሚ እንዲከለስ ተደርጓል።

በሄክታር የሚገኘው የምርት መጠን በየዓመቱ የ4 በመቶ ዕድገት በማሳየት 37 ኩንታል የደረሰ ሲሆን፥ በዘርፉ የተሰማራው ኃይል ዕውቀትንና ቴክኖሎጂን ከላቡ ጋር አቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ያሳያል።

ዛሬ ላይ የመንግሥት ፖሊሲና የሕዝቡ ቁርጠኝነት ኢትዮጵያን ከጠባቂነት ቀንበር አውጥቶ ወደ ብልጽግና ጎዳና እንድትራመድ ያደረገ ሲሆን፥ ስሟን በታሪክ መዝገብ ላይ በድህነት ሳይሆን በስንዴ ምርትና በምግብ ሉዓላዊነት ዳግም እየጻፈች ትገኛለች፡፡

በዮናስ ጌትነት