የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የባሕር መስመሮች ላይ ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማጠናከር …

By Abiy Getahun

May 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና በዓለም መድረክ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ ተግባራዊ እያደረገ ያለው አዲስ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

ከለውጡ በፊት የነበረው የውጭ ግንኙነት በውስጣዊ መከፋፈልና በስትራቴጂክ ዕይታ ማጣት ምክንያት ላልቶ የነበረ ሲሆን÷ አሁን ላይ የ130 ሚሊየን ሕዝብ የጋራ ጋሻና ኩራት እንዲሆን የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።

ቀደም ሲል የነበረው አሰራር ሀገሪቱን ለውጭ ዕዳና ለእርዳታ ጥገኝነት አጋልጦ የቆየ ቢሆንም የአሁኑ የዲፕሎማሲ መስመር ግን ኢትዮጵያን ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት አሻግሯታል።

በተለይም የባሕር በር ፍላጎትን በተመለከተ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ታፍኖ የነበረውንና ሀገራችንን “የየብስ እስረኛ” አድርጎ የቆየውን ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

ኢትዮጵያ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆኗ ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷ አደጋ መሆኑን በመረዳትም ፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ማቅረብ ተችሏል። ይህ ጥረት የንግድ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የባሕር መስመሮች ላይ ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማጠናከር ያለመ ነው።

የመደመር መንግሥት በቀጣይ የባሕር ኃይልን በማደራጀትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በትኩረት ይሰራል።

የአፍሪካ ቀንድ የኃያላን ሀገራት የፉክክር መድረክ እየሆነ ባለበት በዚህ ወቅት የመደመር መንግሥት “አጋር ማብዛት” ላይ ያተኮረ ተራማጅ የዲፕሎማሲ ፍልስፍናን እየተከተለ ይገኛል።

የዚህ ስትራቴጂ ውጤትም ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS+) ሙሉ አባል እንድትሆን አስችሏታል። ይህም ለሀገሪቱ ሰፊ የገበያ አማራጭ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የፈጠረ ታሪካዊ ስኬት ነው።

በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የስምምነት ማዕቀፍ (CFA) ወደ ተግባር መግባት ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያላትን የመሪነት ሚና በተጨባጭ ያሳዩ ድሎች ናቸው።

የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት መርህ ከሀገራዊ ክብር ባለፈ የዜጎችን ክብርና ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ሲሆን÷ ሉዓላዊነት የሚከበረው ዜጎች በኢኮኖሚ ሲጠነክሩና በምግብ ራሳቸውን ሲችሉ መሆኑን ያምናል።

በዚህም መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብታቸው ተከብሮ የሀገራቸው የልማት አጋር የሚሆኑበትን ሥርዓት ዘርግቷል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትና በዓለም የምግብ ፕሮግራም ቦርድ ውስጥ መሪ ሆና መመረጧም የሀገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ አቅም ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ወደፊትም መንግሥት የጀመራቸውን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያን ከተረጂነትና ከዕዳ ቀንበር ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማውጣት ግብ ጥሏል።

የጎረቤት ሀገራት ግንኙነትን በጋራ ብልጽግና ላይ በመመሥረት ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የሰላምና የኢኮኖሚ ማዕከል እንድትሆን በመስራት ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅምን ከዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር አጣጥሞ በማስኬድ የኢትዮጵያን ክብርና ዝና የሚመጥን የዲፕሎማሲ በላይነትን ማረጋገጥ የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ይቀጥላል።