አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍኤምሲ) ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅም በመቀየር፣ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ሀገሪቱ ያላት ታዳሽ የኃይል ሀብት ዝም ብሎ የሚፈስ ውሃ ሳይሆን በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ውስጥ ዋነኛ ብሔራዊ አቅም ነው፡፡
የኃይል አቅርቦት ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ አብዮቶች፣ ለዲጂታል ኢኮኖሚ እና ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ግንባታ መሠረታዊ ምርጫ እየሆነ መጥቷል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኃይል ማዕከል የማድረግ ራዕይ ተሰንቆ የኢነርጂ ትስስርን እንደ ፖለቲካዊ መተማመኛ መሣሪያ መጠቀም ላይ ትኩረት ተደርጓል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ የገባችውን ቃል በተግባር በመለወጥ ለጎረቤት ሀገራት ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ዋነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ መሆን ችላለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኮይሻ እና ሌሎች ግዙፍ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የቀጣናውን የጋራ ዕድገት የሚያረጋግጡ የትስስር ድልድዮች ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ይህ የታዳሽ ኃይል ልማት እንደ አንድ ቴክኒካዊ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት እና የቀጣናዊ መሪነት ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
የቀጣናዊ ትስስር ማስፋፊያ ሥራዎችን በተመለከተ ከታንዛኒያ ጋር የተጀመረው የኃይል ሽያጭ የሙከራ ፕሮጀክት ትልቅ እመርታዊ ማሳያ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን በማቋቋም ለወደፊት ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል አጠቃቀም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና መሠረቶች ተጥለዋል።
ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በመዘርጋትም ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በኤሌክትሪክ እንድትገናኝ ተደርጓል።
ይህም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገርን የኃይል ዋስትና ለማረጋገጥ የኃይል ምንጮችን ማብዛት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ስትራቴጂ ነው።
አንዳንድ ወገኖች ለጎረቤት ሀገራት የሚደረገውን የኃይል አቅርቦት ኪሳራ አድርገው የሚያንጸባርቁት የተሳሳተ አመለካከት የረዥም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅምን ካለመረዳት የሚመነጭ መሆኑን ሁኔታዎች ያስረዳሉ።
የኃይል ከትስስር የንግድ ልውውጥ ባሻገር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድግ የዲፕሎማሲ መሣሪያ ነው።
ጎረቤት ሀገራት በኢትዮጵያ ኃይል መብራት ሲያገኙ፣ ኢንዱስትሪዎቻቸው ሲንቀሳቀሱ፣ ለብሔራዊ ደህንነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት ትልቅ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
በተመሳሳይ የኒውክሌር ኃይልን ለሕክምና፣ ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ማዋል ኢትዮጵያ ወደ ቴክኖሎጂ ልዕለ-ኃያልነት የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።
የእነዚህ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ቀስ በቀስ መታየት የጀመሩ ሲሆን፤ ለጎረቤት ሀገራት ከሚቀርበው ኃይል የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ለሀገራዊ ልማት መዋል ጀምሯል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያላት ተፅዕኖም አድጓል፤ የኢነርጂ ዘርፉ መስፋፋት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችም እንደ ጀርባ አጥንት ሆኖ በማገልገል ላይ ሲሆን፤ ይህ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ “የመደመር” ፍልስፍና ውጤት አንዱ ሀገር ለሌላው የህልውና ዋስትና የሚሆንበትን ሥርዓት እየገነባ ነው።
መንግሥት የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ግልጽ ዕቅዶችን አስቀምጦ የኃይል ሽያጭ ትስስርን ከአፍሪካ ቀንድ አሻግሮ እስከ ሰሜን አፍሪካና አውሮፓ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፤ ይሰራል።
እንዲሁም ከውሃ ኃይል በተጨማሪ በፀሐይ፣ በነፋስና በጂኦተርማል ኃይል ማመንጫዎች ላይ በስፋት ኢንቨስት በማድረግ አስተማማኝ የኃይል አማራጮችን የመፍጠር ሥራም ይጠናከራል።
ኢትዮጵያ የራሷን ፍላጎት መቶ በመቶ አሟልታ የቀጣናው ዋነኛ የኃይል “ባንክ” እንድትሆንና ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ የማድረጉ ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል።