የሀገር ውስጥ ዜና

ሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ጥቃት መከላከል በሚያስችል ደረጃ ላይ ነው – ጄኔራል አበባው ታደሰ

By Adimasu Aragawu

May 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ጥቃት መከላከል በሚያስችል ደረጃ ላይ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፡፡

ጄኔራል አበባው በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የግዳጅ ቀጣና ተገኝተው እንዳሉት÷ ዕዙ ከታሪካዊ ጠላቶቻችንም ይሁን ከባንዳዎች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን መመከት በሚያስችል የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ሰሜን ምዕራብ ዕዝ መከላከያ የሰጠውን ግዳጅ በላቀ ጀግንነት እየፈፀመ የመጣ የተቋማችን አስተማማኝ ዕዝ ነው ብለዋል፡፡

የሕወሓትን ሀገር የማፍረስ ተከታታይ ወረራ በመመከትና ሀገርን በማፅናት ትልቅ ሚና የነበረው ጠንካራ ዕዝ ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ሰሜን ምዕራብ ዕዝ በአማራ ክልል ግጭትና ሁከት ለመፍጠር በተንቀሳቀሰው የሀገር ውስጥ ባንዳ በሆነው ፅንፈኛው ቡድን ላይ ጠንካራ ርምጃ በመውሰድ ወገን የኮራበትና ጠላት ያፈረበትን ከፍተኛ ስራ መስራቱንም ገልጸዋል፡፡

የአባቶቻችሁን የጀግንነት ታሪክ እና አደራ ተቀብላችሁ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ላደረጋችሁት እና በቀጣይም ለምታደርጉት ተጋድሎ ኢትዮጵያ እና ተቋሙ ይኮሩባችኋል ሲሉም ለሠራዊት አባላቱ ተናግረዋል።

ምንጊዜም የኢትዮጵያ አለኝታ የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያ ወደ እድገት የምታደርገው ጉዞ እንዲፋጠን፣ የሕዝቦቿን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው÷ ዕዙ ከተቋሙ የተሰጡትን ተደራራቢ ግዳጆች ተቀብሎ በፅናትና በቁርጠኝነት ፈፅሟል ነው ያሉት፡፡

ለቀጣይ ግዳጅና ተልዕኮም ዝግጁነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ መሆኑን መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።