አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የተወለደው ድምጻዊ አሊ ቢራ በሙዚቃ ሥራዎቹ ለጭቁኖች ሲታገል እንዲሁም ብዙዎችን ሲያዝናና ሲያስደስት የኖረ ነው፡፡
አሊ ቢራ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ለስድስት አስርት ዓመታት በድምጻዊነት፣ ግጥምና ዜማ ደራሲነት ከፈር ቀዳጅ አርቲስቶች ዋነኛው ነው፡፡
በአፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ አፋርኛ፣ ዓረቢኛና ሶማሊኛ የመሳሰሉ ቋንቋዎች መዝፈኑ የሚነገረው አሊ ቢራ÷ ከባህር ማዶም በስፓኒሽ፣ በስዊዲሽ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች እንደሚዘፍን የታሪክ ማህደሩ ያሳያል፡፡
ስለ ፍቅር፣ ትምህርት፣ ባህል፣ እርቅና ሰላም፣ ሰብዓዊ መብት እና እኩልነት በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ያቀነቀነው ድምጻዊው በስራዎቹ የአድማጩን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡
አሊ ቢራ በ1954 በትወልድ ከተማው ድሬዳዋ አፍረን ቀሎ አማካይነት በተቋቋመው ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን በመግባት የድምጻዊነት ሕይወትን መጀመሩ ይነገራል፡፡
ምንም እንኳን ወላጆቹ ያወጡለት ስም አሊ መሐመድ ሙሣ ቢሆንም “ቢራ ዳ በሪኤ” ከሚለው የመጀመሪያ አልበም መውጣትን ተከትሎ አሊ ቢራ የሚል መጠሪያ አግኝቷል፡፡
267 ሙዚቃዎችን በ13 አልበሞቹ ውስጥ በማካተት ለሙዚቃ አፍቃሪው ጆሮ ያደረሰው አሊ ቢራ÷ ከተወዳጅ ሙዚቃዎቹ መካከል “ዋ መሊ ኑ ዲቤ”፣ “ጃላሉማ ቴቲ”፣ “በርኖታ”፣ “ከራ መና አባ ገዳ ኤሳ” እና “አማሌሌ” የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በዘፈኖቹ ፍቅርን፣ እርቅን፣ ሰላምና መተሳስብን አጉልቶ መሳየት የቻለው አሊ ቢራ÷ በሥራዎቹም ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው ከ100 በላይ ሽልማቶችን ወስዷል።
በፈጠረው ከፍተኛ ተጽዕኖም የጅማና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት አበርክተውለታል።
ከዚህም ባሻገር የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በስሙ የተሰየመ ሲሆን÷ በአዳማ ከተማ መንገድ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ደግሞ ፓርክ በስሙ ተሰይሞለታል።
የክብር ዶ/ር አሊ ቢራ ከፍተኛ ህመም አጋጥሞት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለደ በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የድምጻዊ አሊ ቢራን ጨምሮ ለሀገራቸው ሰላም፣ ለሀገር ግንባታ፣ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ለፍትህ፣ ለነፃነትና እኩልነት ላቀነቀኑ የሀገር ባለውለታ አርቲስቶች የተሰራውን መታሰቢያ መመረቃቸው ይታወሳል።
በአቤል ነዋይ