የሀገር ውስጥ ዜና

በገበያ ላይ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ያደረጉ 13 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

By Adimasu Aragawu

May 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በገበያ ላይ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ያደረጉ 13 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ተከሳሾቹም 1ኛ አቶ ዲባራ ፉፋ፣ 2ኛ አቶ ሹምአለም ብርሃኔ፣ 3ኛ አቶ እስጢፋኖስ ጌትነት፣ 4ኛ አቶ ይላቅ አወቀ፣ 5ኛ አቶ አበላ ግዛው፣ 6ኛ አቶ ጌታቸው አሞኘ፣ 7ኛ ወ/ሮ በረከት ወርቁ፣ 8ኛ አቡሽ አያለ ገነት፣ 9ኛ አቶ ይልቃል የኔሰው፣ 10ኛ የኛ ፔትሮሊዮም ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ 11ኛ አቶ እስማለም ምህረቱ፣ 12ኛ አቶ አባይነህ አወል እና 13ኛ አቶ ብስራት አበባው ናቸው።

ተከሳሾቹ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ነዳጅና ነጭ ናፍጣ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ በማድረግ በገበያ ላይ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

የክስ መዝገቡ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርቧል፡፡

1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች እንደ ቅደምተከተላቸው የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ክትትል ባለሙያ ከኩባንያዎች በቀጥታ በመግዛት ለሚጠቀሙ ተቋማት የፍቃድ አሰጣጥ መመሪያ መተላለፋቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡

ሦስቱ ተከሳሾች በግል የሥራ ዘርፍ ከተሰማራችው 7ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር 466 ሺህ 58 ሊትር ነጭ ናፍጣ ያለአግባብ እንድታገኝና በኮንትሮባንድ ለወርቅ አምራቾች እንድትሸጥ ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በመንግሥት ላይ ከ8 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስና በገበያ ላይ እጥረት እንዲከሰት በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ መገልግል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ሲል ዐቃቤ ህግ አስረድቷል፡፡

በሌላ በኩል በ2ኛ ክስ 1ኛ፣ 6ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር 8ኛ ተከሳሽ በድምሩ ከ1 ሚሊየን 284 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ያለአግባብ እንዲያገኝ በማድረግ በመንግሥት ላይ ከ22 ነጥብ 59 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስና የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርገዋል ብሏል፡፡

በዚህም 1ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን ያለአግባብ በመገልግል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

በ3ኛ ክስ 9ኛ ተከሳሽ (የኛ ፔትሮሊዮም ኃ/የተ/የግ/ማህበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ) ከህግ አግባብ ውጪ የነዳጅ አከፋፋይነት ፍቃድ እንዲያገኝ በማድረግ በመንግሥት ላይ ከ21 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ላይ ጉዳት መድረሱን ክሱ ያመለክታል፡፡

በዚህም መሰረት 1ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት እንዲሁም 9ኛ ተከሳሽ በልዩ ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልግል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

በ4ኛው ክስ ላይ 11ኛ፣ 12ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች የነዳጅ ጭነትና ግዥ ሀገር አቀፍ የነዳጅ ሰንሰለት ስርዓትን በመጣስ በአጠቃላይ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ መንግሥት እንዳይቆጣጠረው ማድረጋቸውን ክሱ አመልክቷል፡፡

በዚህም መንግሥት ድጎማ ያደረገበትን ነዳጅ ከጅቡቲ በመጫን 17 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይና በገንዘብ የማይገመት ጉዳት በማድረስ በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግሥትን ሥራ በማይመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በ5ኛው ክስ ላይ 11ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 346 የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1359/2017 አንቀጽ 51(1)(መ) እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመሪያ ቁጥር FXD/04/2024” አንቀጽ 22.8.5/ለ ስር ላይ የተመለከተውን በመተላለፉ ክስ ተመስርቷል።

በዚህም ተከሳሹ በዕለቱ ለመያዝ ምንም አይነት ፍቃድ ሳይኖረው በቀን 30/07/2018 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 10፡30 ሰዓት ሲሆን፤ ከፍርድ ቤት በስልክ በተገኘ የብርበራ ፍቃድ ቂርቆስ ክ/ከተማ በሚገኘው የመኖሪያ ቤቱ እና በቢሮ ላይ በተደረገ ብርበራ 1ኛ 58 ሺህ 503 የአሜሪካን ዶላር 2ኛ 6 ሺህ 250 ዩሮ 3ኛ 630 የእንግሊዝ ፓወንድ አስቀምጦ የተገኘ በመሆኑ በፈጸመው በህገ ወጥ መንገድ የውጭ ሀገር ገንዘብ ያለፈቃድ መያዝ/ማስቀመጥ ወንጀል ተከሷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያ ለመስማት ለግንቦት 10 ቀጠሮ መያዙ ተገልጿል።

በመቅደስ ከበደ