አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ጦርነት ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ሊቆም የሚችልበት ተስፋ እየታየ ነው።
ሁለቱ ሀገራት ወደ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ የሚመጡበት ከፍተኛ እድል መታየቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ዋሽንግተን እና ቴህራን ቢያንስ ለጊዜው ጦርነት እንዲቆም፣ በሆርሙዝ ሰርጥ ያለው ውጥረት ጋብ እንዲል እና ለሰፊ ውይይት መንገድ የሚከፍት ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ነው የተሰማው።
ይህ ጥረት ግጭቱን ለአጭር ጊዜ ሊያቆመው ይችላል የሚለው ተስፋ ከፍ ያለ ቢሆንም የኢራን ኒውክሌር የማበልጸግ ጉዳይ፣ ማዕቀቦችን የማንሳት እና ሌሎች ቀጣናዊ አለመግባባቶች መፍትሔ ሳያገኙ ይቀጥላሉ።
ይሁን እንጂ በዚህ መካከል ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን ለአጭር ጊዜ ለማቆም በሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ላይ ለመስማማት መቃረባቸው ተሰምቷል።
ኢራን በአሜሪካ የቀረበውን 14 ነጥብ የውሳኔ ሐሳብ የያዘ የድርድር ዕቅድ ስትገመግም ቆይታለች።
ባለ አንድ ገጹ የመግባቢያ ስምምነት በዝርዝር ለሚካሄድ የኒውክሌር ድርድር በማዕቀፍነት የሚያገለግሉ 14 ነጥቦችን መያዙ ታውቋል።
ኢራን ኒውክሌር የማበልጸግ ተግባሯን እንድታቆም ስለማድረግ፣ ማዕቀቦችን ስለማንሳት እና በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚደረግ ነጻ ጉዞን መመለስ የሚሉት ከስምምነት ነጥቦቹ መካከል ይገኙበታል።
በብርሃኑ አበራ