የሀገር ውስጥ ዜና

የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ በትኩረት እየተሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Mikias Ayele

May 08, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ምክንያት የኑሮ ውድነት ችግሮች እንዳይባባሱ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ፡፡

ከንቲባዋ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የገበያ ማረጋጋትና ኑሮ ውድነትን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የምርት አቅርቦትን መጨመርና የንግድ ሰንሰለቱን የሚያሳጥሩ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ያሉት ከንቲባዋ፤ ችግሩ በሀገር ውስጥ  ሁኔታ ብቻ እንደማይወሰን አብራርተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ እና በሀገር ውስጥ ተፅዕኖ ሳቢያ የሚከሰቱ የገበያ መዛባቶች የሚያስከትሉት የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ ለማድረግ መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የሀገር ውስጥ የምርት አቅርቦትን መጨመር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መጠን በመቀነስ ተኪ ምርቶችን ማምረት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመዲናዋ በሚደረጉ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዘገባቸውን ጠቅሰው፤ በህገወጥ ተግባራት ላይ በተሰማሩ 18 ሺህ 400 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

የንግድ ኮርፖሬሽን በማቋቋምና ድጋፍ በማድረግ ምርቶች ለህዝቡ እንዲቀርቡ በመደረጉ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል ማለታቸውን የከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡