አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብፅ የሱዳንን ሰላምና ዕድገት እንደ ቀጥተኛ ስጋት ነው የምትመለከተው አሉ ሱዳናዊ ጸሐፊና ተንታኝ ናስር ሳቲ (ዶ/ር)።
ከሰሞኑ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ያነሳችውን ክስ ተከትሎ ሱዳናዊው ጸሐፊ ናስር ሳቲ (ዶ/ር) በሱዳንና በግብፅ መካከል ያለውን የፖለቲካና የስትራቴጂ ግንኙነት በስፋት ዳሰዋል፡፡
ጸሐፊው ካርቱም ከነጻነት በኋላ ለካይሮ ያሳየችውን የፖለቲካ ተጠላይነት በመተቸት ይህ ሁኔታ የቀጣናው ደህንነትና ጂኦፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አንስተዋል።
ግብፅ በሱዳን ላይ ያላት ፍላጎት ግልፅና የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ሱዳን በወርቅ፣ በውሃ ሃብትና በሰፊ የእርሻ መሬቷ በመጠቀም በራሷ የቆመች ጠንካራ ሀገር እንድትሆን እንደማትፈልግ ገልጸዋል።
ግብፅ የሱዳንን እድገት እንደ ቀጥተኛ ቀጣናዊ ስጋት እንደምትመለከት አንስተው፤ ሱዳን ከጠነከረች ራሷን የቻለች የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቋም ያላት ሀገር ትሆናለች የሚል ፍራቻ እንዳላት ጠቁመዋል።
ካይሮ ሱዳንን ለብዙ ዓመታት በፖለቲካና በስትራቴጂ ተፅዕኖዋ ስር ለማቆየት በተደጋጋሚ እንደሰራች አብራርተዋል፡፡
ግብፅ ሱዳንን በቀጣናዊ ጉዳዮች ውስጥ እንደመሳሪያ መጠቀም ትፈልጋለች፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ብለዋል።
ግብፅ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ግጭት ከመግባት ይልቅ ሱዳን ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታበላሽ ማድረግ የዘወትር መሻቷ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በታሪክ ግብፅ ከድንበሯ ውጪ በገባችባቸው ጦርነቶች ከባድ ኪሳራ እንደደረሰባት አስታውሰው፤ በኢትዮጵያም ይህ አጋጥሟት እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ግብፅ በሱዳን ላይ የምታራምደውን ያልተገባ ፖሊሲ ያወገዙት ጸሐፊና ተንታኙ፤ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መልማትና መጠቀም እየቻለች በተቃራኒው ከጎረቤት ጋር መልካም ግንኙነት እንዳይኖራት ሴራ በመሸረብ ተጠምዳለች ነው ያሉት፡፡
ይህ ድርጊት የውጪ ከበባ በመሞከር ብቻ አያበቃም፣ ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም እንዳይኖራት እና ጊዜ አግኝታ ኃብቷን አልምታ እንዳትበለፅግ የዘወትር ፍላጎቷ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝብ የጎረቤት ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚገነዘቡ፣ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ብዙ ግዜ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ግብፅ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ግጭት የማስገባት ፍላጎት ቢኖራትም፣ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ወንድማማች እና እህትማማች በመሆናቸው ይህ እንዳልተቻላት አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት እንደሚሰጠው ሁሉ፣ የሱዳን መንግሥትም በብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ገለልተኛ የውጭ ፖሊሲ እንዲከተል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሱዳን በቀጣናው ውስጥ በራሷ ፍላጎትና ጥቅም መሰረት የምትንቀሳቀስ ሀገር መሆን እንዳለባትም አሳስበዋል።
በአሚር በድሩ