አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ ለማቆየትና ሕዝባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያን በ2023 ዓ.ም የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ግብ የተያዘ ሲሆን፥ በ2040 ደግሞ ከአፍሪካ ሁለት ታላላቅ የኢኮኖሚ ኃይሎች አንዷና ከዓለም 20 ቀዳሚ ኢኮኖሚዎች ተርታ እንድትሰለፍ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ይህ ራዕይ በዋናነት በዜጎች ተጠቃሚነት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በምግብ ዋስትና እና በኢንዱስትሪ ልማት ላይ የተመሠረተ ነው ።
መንግሥት ከለውጡ በፊት የነበሩ መዋቅራዊ ስብራቶችን ለመጠገንና የመፈጸም አቅምን ለማሳደግ ባደረገው ጥረት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለፍጻሜ ማብቃቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እና ከተማን የማዘመን ፕሮጀክቶች የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም በተግባር ያሳዩ ስኬቶች ናቸው።
እነዚህ ውጤቶች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበረውን ውስብስብ ቢሮክራሲ በመስበር ውጤት ተኮር አሠራርን ለማስፈን የተደረጉ ጥረቶች ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ።
የኢኮኖሚውን ዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በማመን ለ60 ዓመታት ያገለገለውን የንግድ ሕግ እንዲሻሻል አድርጓል።
የባንክና የካፒታል ገበያ ዘርፎችን ለውድድር ክፍት ማድረጉ ቀደም ሲል በዕዳ ተተብትቦ የነበረውን ኢኮኖሚ ወደ ምርታማነትና ወደ ምንዳ ለመቀየር ያስቻለ ድፍረት የተሞላበት ርምጃ ያደርገዋል።
በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው ውጤት ሀገሪቱ በምግብ ራሷን እንድትችል ብቻ ሳይሆን ምርትን ወደ ውጭ እንድትልክም በር ከፍቷል።
ከዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አንጻር መንግሥት አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን (ስታርታፕ) የሚያበረታቱ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለወጣቶች ምቹ የሥራ ከባቢ እየፈጠረ ይገኛል።
በተጨማሪም በ30 ቢሊየን ዶላር ወጪ የሚገነቡት “ሰባቱ የጉባ ብሥራቶች” ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና የዜጎችን አኗኗር በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥ ታስበው ወደ ተግባር ገብተዋል።
እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ክብሯን ከፍ የሚያደርጉ እንደሆኑ ታምኖባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት ተርታ ተሰልፏል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን፥ በዚህ ዓመት ደግሞ ይህ ዕድገት ከ10 ነጥብ 2 በመቶ በላይ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል።
መንግሥት ድንገተኛ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ተግዳሮቶችን የመቋቋም አቅሙን በማሳደግ ወደፊት እንዲጓዝ ማድረጉ እንደ ስኬት ይወሰዳል።
ይህ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሀገሪቱን ወደ አስተማማኝና አካታች ብልፅግና ለመውሰድ መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ነው።