አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሪታኒያ ከሆርሙዝ ሰርጥ ተልዕኮ ጋር በተገናኘ ኤችኤምኤስ ድራጎን የተሰኘ የጦር መርከቧን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ማንቀሳቀስ ጀመረች፡፡
ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ ከሰሞኑ በሆርሙዝ ሰርጥ የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦችን ከጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችል ወታደራዊ ተልዕኮ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች እንደገለጹት ወታደራዊ ተልዕኮው በቀጣናው የቀጠለው ጦርነት እስከሚያበቃ ድረስ የሚቆይ ሲሆን፥ ፈረንሳይ ባሳለፍነው ረቡዕ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን ወደ ቀይ ባህር መላኳ የሚታወስ ነው፡፡
የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት እንዳስታወቀው፥ የሀገሪቱ ጦር ኤችኤምኤስ ድራጎን የተሰኘውን የአየር መቃወሚያና ጸረ ሚሳኤል የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ይህ አውዳሚ የጦር መርከብ ኢራን ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር የገባችበትን ጦርነት ተከትሎ ቆጵሮስን ከጥቃት ለመጠበቅ ወደ ምስራቅ ሜድትራንያን ተልኮ እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡
ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ በሆርሙዝ ሰርጥ በተለይም የንግድ መርከቦች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲያልፉ ለማድረግ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሁለቱ ሀገራት እቅድ የኢራንን ትብብር የሚሻ ቢሆንም፤ በርካታ ሀገራት ተልዕኮውን ለማገዝ ፍቃደኛ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአቤል ነዋይ