ስፓርት

ኤልክላሲኮ – ባርሴሎና የቡድን አንድነቱን ካጣው ሪያል ማድሪድ…

By Adimasu Aragawu

May 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ35ኛ ሳምንት የስፔን ላሊጋ መርሐ ግብር ባርሴሎናን ከሪያል ማድሪድ የሚያገናኘው ኤልክላሲኮ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት በካምፕ ኑ ይደረጋል፡፡

በቀደሙት ዓመታት ኤልክላሲኮ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት መርሐ ግብር ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በርስ ግንኙነት በቀደሙት ዓመታት የነበረውን ከፍተኛ ፉክክሩን እያጣ መጥቷል፡፡

የመጀመሪያው የኤልክላሲኮ ጨዋታ የተደረገው በፈረንጆቹ 1902 ሲሆን ጨዋታውን ባርሴሎና 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ሪያል ማድሪድ ከፈረንጆቹ 1962 እስከ 1965 ባርሴሎናን በሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ በኤልክላሲኮ ረጅም የማሸነፍ ክብረወሰን ባለቤት ነው፡፡

በፈረንጆቹ 1943 ሪያል ማድሪድ ባርሴሎናን 11 ለ 1 ያሸነፈበት የኮፓ ዴል ሬይ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ በኤልክላሲኮ ታሪክ ሰፊ ውጤት የተመዘገበበት ነው፡፡

በ2024/25 የውድድር ዓመት ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች የባርሴሎና የበላይነት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ባርሴሎና በዚህ የውድድር ዓመት ከምሽቱ ተጋጣሚው ሪያል ማድሪድ በ11 ነጥብ ርቆ በ88 ነጥብ የስፔን ላሊጋን እየመራ ይገኛል፡፡

ባርሴሎና ከዛሬው ጨዋታ አንድ ነጥብ የሚያገኝ ከሆነ ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት የላሊጋው ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

በአሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ የሚመራው የካታላኑ ክለብ ለተከታታይ ሁለተኛ የውድድር ዓመት የላሊጋው ሻምፒዮን ለመሆን ከጫፍ ደርሷል፡፡

ያለፉትን 10 ጨዋታዎች በላሊጋው ድል ያደረገው ባርሴሎና አሸናፊነቱን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡

ለተከታታይ ሁለተኛ የውድድር ዓመት ከላሊጋው ዋንጫ ውጪ ለመሆን የተቃረበው ሪያል ማድሪድ የቡድኑን አንድነት ባጣበት ወቅት ከምን ጊዜም ተቀናቃኙ ባርሴሎና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ምን ያሳያል የሚለው ተጠባቂ ነው፡፡

የቡድኑ ተጫዋቾች የገቡበት የእርስበርስ ግጭትና በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ኪሊያን ምባፔ ይልቀቅልን በማለት ያቀረቡት ጥያቄ የሎስብላንኮዎቹ ወቅታዊ ፈተና ሆነዋል፡፡

ከሰሞኑ በሪያል ማድሪድ የመልበሻ ክፍል ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበ ሲሆን፥ ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ እና ኦሪሊየን ቹሃሚኒ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡

ቫልቬርዴ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በደረሰበት ጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሲሆን፥ ቹሃሚኒ በበኩሉ በምሸት የማድሪድ ስብስብ ውስጥ እንደሚካተት አሰልጣኙ አረጋግጠዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ባርሴሎና አራቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሪያል ማድሪድ በአንዱ ድል አድርጓል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ