አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእናትን ውለታ የሚመጥን ስጦታ ባይኖርም ፍቅርና መስዋዕትነቷን ለመዘከር በዛሬው ዕለት የእናቶች ቀን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ታስቦ ይውላል።
ስለ እናት ብዙ ተዚሟል፣ ስንኝ ተቋጥሯል፤ ከእነዚህ ውስጥ በተለይም ዘመን አይሽሬው የብዙነሽ በቀለ የእናት ውለታዋ ሙዚቃ ይጠቀሳል፡፡
ብዙነሽ በዚህ ዜማዋ እንዲህ ስትል ታቀነቅናለች…
የእናት ውለታዋን ባወሳ እወዳለሁ፣ ደግነቷ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ፣ ወላጅ እናት እኮ ፍፁም በመንፈሷ፣ ልጇን ትወዳለች አብልጣ ከራሷ፡፡
ዘጠኝ ወር በሆድዋ፣ ከዚያም በጀርባዋ፣ ጡቷን እያጠባች እኔን ማሳደግዋ፣ ዘወትር ይሰማኛል የእማዬ ድካሟ፣ ጥራ በማሳደግ በሴትነት አቅሟ፡፡
የእናት ውለታዋን ባወሳ እወዳለሁ፣ ደግነቷ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ፣ ወላጅ እናት እኮ ፍፁም ሳትሰለች፣ ከራሷ አስበልጣ ልጇን ትወዳለች፡፡
አባቴ ሞቶብኝ በሕፃንነቴ፣ ደክማ አሳደገችኝ ብቻዋን እናቴ፡፡ ሳይርበኝ ሳይጠማኝ ወይም ሳልታረዝ፣ ነው ያሳደገችኝ እማምይ…
የእናት ውለታዋን ባወሳ እወዳለሁ፣ ደግነቷ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ፣ ወላጅ እናት እኮ ፍፁም ሳትሰለች፣ ከራሷ አስበልጣ ልጇን ትወዳለች፡፡
እናቱን የማይወድ ሰው አለ ቢሉኝ፣ ሰው ነው አልለውም አውሬ ነው ባይ ነኝ፣ የዋሂቷ እናቴ እኔን ወላጅቷ፣ እጅግ ይሰማኛል እውነተኛነቷ ::
የእናት ውለታዋን ባወሳ እወዳለሁ፣ ደግነቷ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ፣ ወላጅ እናት እኮ ፍፁም ሳትሰለች፣ ከራሷ አስበልጣ ልጇን ትወዳለች፡፡