የሀገር ውስጥ ዜና

የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተስፋፉ ነው – አቶ ጥላሁን ከበደ

By Mikias Ayele

May 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተስፋፉ ነው አሉ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በወላይታ ዞን ሆቢቻ ወረዳ የተገነባውን የብዝሃ ቀበሌ ንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተስፋፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በላይ በሆነ ወጪ በአምስት ከተሞች የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ባለፉት አስር ወራት ብቻ 65 አነስተኛና መካከለኛ ፕሮጀክቶች ገንብቶ በማጠናቀቅ ከ418 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ከፍተኛ የሕዝብ ጥያቄ ላለባቸው የልማት ስራዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ መንግሥት በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ መንግሥት ቃል የገባቸውን መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየፈታ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ማህበረሰቡ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበው፤ የውሃ ምንጭ ያለባቸው አካባቢዎች የተፈጥሮ እርጥበት ሳይለቁ እንዲቆዩ ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ መጠናከር አለበት ነው ያሉት።

በመለሰ ታደለ