አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት በጤና ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባዋ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን ኦሲስ አጠቃላይ ሆስፒታል በዛሬው ዕለት መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አዲስ አበባ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው ሆስፒታልም ለነዋሪዎች፣ በሪፈር ለሚመጡ እና ወደ መዲናዋ ለሚመጡ ዓለም አቀፍ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘመናዊ አገልግሎት በመስጠት በዘርፉ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።
ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሰራ ይገባል ያሉት ከንቲባዋ÷ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው÷ ከተማዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ማሟላትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ በዚህ ረገድ አቅም መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
የሆስፒታሉ ባለቤት አሚር በድሩ ሆስፒታሉ ከሌሎች የአጎራባች ሀገራት የሚመጡ ታካሚዎችን በመቀበል በሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ ውስን የሆኑ የህክምና አገልግሎቶች በተለይም የልብ ቀዶ ህክምና፣ የካንሰር ህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ በስፋት ይሰራል ነው ያሉት።
ሆስፒታሉ ዓለም የደረሰበትን የህክምና መሳሪያዎች በማሟላት የውስጥ ደዌ፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የህፃናትና የጨቅላ ህጻናት፣ ጠቅላላ ቀዶ ሕክምና እንዲሁም የልብ እና የነርቭ ሕክምናዎችን ይሰጣል ተብሏል።
በተጨማሪም አስተኝቶ ማከም፣ የተሟላና እጅግ ዘመናዊ ላቦራቶሪ፣ ኤምአርአይ፣ ሲቲ ስካን፣ ኢንዶስኮፒና ኮሎኖስኮፒ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
እንዲሁም የካንሰር፣ የአጥንት፣ የኩላሊት፣ የሕብረሰረሰር፣ የጽኑ ሕሙማን፣ የኩላሊት ጠጠር ማውጣት፣ የአልትራሳውንድ ምርመራ፣ የኩላሊት ዕጥበት፣ የሥነ ልቦና ህክምናዎችን፣ የድንገተኛና ትራውማ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚሰጥም ተመላክቷል።
በቅድስት አባተ